ቀጥታ፡

መንግስት እየወሰደ ላለው ህግ የማስከበር ዘመቻ ማንኛውንም ድጋፍ እናደርጋለን…የሃዋሳ የከተማ አመራሮች

ሀዋሳ  ህዳር 05/2013 (ኢዜአ) መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በመደገፍ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ገለጹ።

አመራሮቹ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሕይወት ዋጋ በመክፈል ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል። 

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ በጦር ግንባር ዋጋ እየከፈለ ላለው ሰራዊት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አመራሮቹ ዝግጁ ናቸው።

አመራሩ አጋርነቱን ከሚገልጽባቸው ተግባራት አንዱ ደም መለገስ በመሆኑ ሁሉም የከተማ አስተዳሩ አመራሮች መሳተፋቸውን የገለፁት ምክትል ከንቲባው ይህም ማህበረሰቡ ድረስ የሚወርድ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

“የከተማዋ ነዋሪዎች ባካሄዱት ሰልፍም ሆነ በተለያዩ መንገዶች መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ እየደገፈ እንደሚገኝ ገልፀው ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ድጋፎችን እናደርጋለን” ብለዋል፡፡

“የአትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሀገሩ ዳር ድንበርና ህልውና ደሙን ሲያፈስ የኖረ ነው” ያሉት የሀዋሳ ከተማ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ወርቁ “በወገኖቹ መካከል ሳለ ባልጠበቀው መንገድ የደረሰበት ጥቃት እጅግ አሳዝኖናል” ብለዋል።

ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ደማቸውን መለገሳቸውንና ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመቆም ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ህዝቡ በዚህ ረገድ ከመንግስት ጎን ከመቆሙም ባሻገር አካባቢውን ከፅንፈኛው ቡድን ተላላኪዎች በመጠበቅ ሠላሙንና አንድነቱን ማስቀጠል እንዲችል የማነቃነቅና የማስተባበር ሥራም እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም