በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን ከ313 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን ከ313 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ ህዳር 6/2013 (ኢዜአ) "ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግድብ የብርቱ ህዝቦች ፣የአንድነታችን ፣የአብሮነታችን ማሳያ የብልጽናችን መሰረት በመሆኑ እንደ ህውሃት አይነት ባንዳዎች ከግድቡ ፍጻሜ ለአፍታም አያስቆሙንም" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ ።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን ከ313 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ ።
ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለየካ ክፍለ ከተማ አስረክበዋል ።
በዋንጫ ርክክቡ ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት እስካሁን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎች ከታቀደው በላይ በመሰብሰብ ላይ መሆኑን ገልጸዋል ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የብርቱ ህዝቦች ፣የአንድነታችን ፣የአብሮነታችን ማሳያ የብልጽናችን መሠረት በመሆኑ እንደህውኃት አይነት ባንዳዎች ከግድቡ ፍጻሜ ለአፍታም አያስቆሙንም ሲሉ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።
የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ይታያል ደጀኔ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ በተረከበ በሁለት ሳምንት ጊዜ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ባለሀብቶች እና ህብረተሰቡን በማስተባበር ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ከ313 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ መሰብሰቡን ገልጸዋል ።
ዋንጫው በክፍለ ከተማው ቆይታ በሚያደርግበት ቀናት በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰው ክህደት አስደንጋጭ ቢሆንም ህብረተሰቡ ለበለጠ እልህና ቁጭት በመነሳሳት ለሃገር አለኝታነቱን አረጋግጧል ብለዋል ።
በዕለቱ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ላደረጉ እና ቦንድ በመግዛት ለተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል ።
በተጨማሪም በአለም አደባባይ ስለህዳሴ ግድብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በተለያዩ አለምአቀፍ ሚዲያዎች ድምጹን ሲያሰማ ለነበረው መሀመድ አል-አሩሲ የእውቅና ሽልማት ከምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተበርክቶለታል ።