የሐጅ ፀሎት ተጓዦች የሚጠየቁት ዋጋ እየናረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሐጅ ፀሎት ተጓዦች የሚጠየቁት ዋጋ እየናረ ነው
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 ከእስልምና እምነት አምስቱ መሰረቶች መካከል አንዱ የሐጅ ፀሎት ነው። በየዓመቱ በሚከወነው በዚህ ስርዓተ-ፀሎት ላይ ከሁለት ሚሊዮን የሚልቅ ምዕመን ከመላው ዓለም ሳዑዲ ዓረቢያ መካ እና መዲና ይሰባሰባሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም በየዓመቱ በዚህ ወቅት ወደ እዚያው ያመራሉ። እንዲያም ሆኖ ግን በሐጅ ፀሎቱ ላይ መሳተፍ የሚሹ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የጉዞና የመስተንግዶ ወጪ በየዓመቱ እየናረባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ዘንድሮ የተጠየቁት ክፍያ እንኳ ከዓምናው በ20 ሺህ ብር አሻቅቧል። ዘንድሮ አንድ የሐጅ ፀሎት አድራጊ 98 ሺህ ብር ክፍያ ይጠበቅበታል። ይህንን የምእመናኑን ጥያቄ በማስመልከት የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተሰጠው ማብራሪያ መሰረትም የጉዞ እና መስተንግዶው ዋጋ የጨመረው የውጭ ምንዛሪ የዋጋ ተመን መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይገልፃል። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስትም በአገልግሎት ክፍያ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ማስከፈል መጀመሩም ለዋጋው መናር ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ክፍል ዋና ስራ እስኪያጅ አቶ ቡሴራ አወል እንደሚሉት አየር መንገዱ ለሐጅ ተጓዦች ብሎ የጨመረው ዋጋ የለም። የአየር ቲኬት ዋጋው ከአምናው የተለየ አይደለም የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በክፍያው ላይ ልዩነት የመጣው የዶላር መጨመርን ተከትሎ የብር የመግዛት አቅም በመቀነሱ ብቻ ነው ብለዋል። ያም ሆኖ አየር መንገዱ ለሐጅ ፀሎተኞች የሚያስከፍለው ዋጋ ከሌሎች መደበኛ ክፍያዎች ጋር በማነፃፀር የሚነሳ ቅሬታ መኖሩንም አቶ ቡሴራ ይናገራሉ። እርሳቸው አንደሚሉት የሃጅ ጉዞ የተለየ ዝግጅት የሚፈልግና ብዛት ያለው የሰው ኃይል የሚሰማራበት ከመሆኑም በላይ ወደ ሳዑዲ የሚሰማሩት አውሮፕላኖችም ምእመናኑን ካደረሱ በኋላ ያለተሳፋሪ የሚመለሱ፤ ምእመናኑን ለመመለስም ባዷቸውን ወደ ሳዑዲ የሚጓዙ ናቸው። የእስልምና ጉዳዮች የሃጅና ኡምራ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ አህመድ ዩሱፍ በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪው ከአቅም በላይ በሆኑ ውጫዊ ምክንያቶች የተከሰተ ነው ይላሉ። የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስትም የተጨማሪ እሴት ታክስ የአገልግሎት ክፍያዎችን ጨምሮ ሌሎች ክፍያዎች ጭማሪ ማድረጉ ለዋጋው መናር ምክንያት ነው ብለዋል። ሆኖም ግን የህብረተሰቡን አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሃጅ ፀሎት ተጓዦች የዋጋ ማሻሻያ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንግድ 78 ዶላር ቀንሶ ለማጓጓዝ በመወሰኑና የእስልምና ጉዳዮችም ከአገልግሎት ክፍያ ላይ ቀንሶ ቀደም ሲል ከተተመነው 98 ሺህ ብር ወደ 93 ሺ ዝቅ እንዲል ማድረጉ ነው የተገለጸው። ከአሁን በኋላ የሚከፍሉት በዚህ ዋጋ እንዲከፍሉና ከዚህ ቀድሞ ለከፈሉት ደግሞ አምስት ሺህ ብር ተመላሽ እንደሚደረግላቸውም በመግለጫው ተገልጿል። በእስልምና እምነት የሐጅ ሰርዓተ-ፀሎትን መከወን ግዴታ የሚሆነው የገንዘብ አቅም ባለው የእምነቱ ተከታዮች ላይ ብቻ ነው።