የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ቡድን ተላቆ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ የመኖር እሴቱን እንዲያጎለብት ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ቡድን ተላቆ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ የመኖር እሴቱን እንዲያጎለብት ተጠየቀ
ጋምቤላ፣ ህዳር 5/2013(ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ ከስግብግቡ የህወሓት ቡድን ተላቆ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ የመኖር እሴቱን እንዲያጎለብት የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጠየቁ።
አመራሮቹ በጋምቤላ ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረኩ የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ሙሉቀን ሀብቱ እንዳሉት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ለ17 ዓመታት ሲዋደቅለት የነበረው የትግል መስመር በተወሰኑ ስግብግቦች አቅጣጫውን ስቶ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።
የትግራይ ህዝብ ባለፉት ዓመታት ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተባብሮ በአብሮነት ጥሮ ግሮ ከማደር ባለፈ በስግብግቡ ቡድን ያገኘው ጥቅም እንደሌለ ገልጸዋል።
ህዝቡ ከስግብግቡ የህወሓት ቡድን ተላቆ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ ሰርቶ የመኖር እሴቱን እንዲያጎለብት ጠይቀዋል።
በተለይም ከጋምቤላ አቃፊው ህዝብ ጋር ያለውን ተባብሮ ሰርቶ የመኖር እሴቱን መጠበቅ እንዳለበትም አመልክተዋል።
የተሳሳተ መስመር የተከተለው ጥቅመኛ የህወሓት ቡድን ሰሞኑን በፈጠረው ችግር ተጠቂ ላለመሆን ህዝቡ ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በአንድነት በመቆም አብሮ የመኖር እሴቱን እንዲያስቀጥል የጠየቁት ደግሞ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር አቶ ሐጎስ ግደይ ናቸው።
የህወሓትን ፈለግ የሚከተሉ ደጋፊዎች ነን ባዮች ባለፉት ዓመታት በጋምቤላ ክልል በርካታ ሀብት ዘርፈው የሄዱ መኖራቸውንና ይህ ጉዳይ እናንተን በጋምቤላ ክልል ስትኖሩ የነበራችሁትን አይመለከትም ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አለማሽ ግደይ በሰጡት አስተያየት ሰሞኑን በሀገር መከላከያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አግባብነት የሌለው አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ አብሮ ከትግራይ ህዝብ ጋር የነበረ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ሠራዊት ድጋፍ እንጂ ይህን መሰል ድርጊት አይገባውም ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት በተቃጣው ጥቃት ማዘናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዘነበ መሐሪ ናቸው።
የትግራይ ህዝብ እየደረሰበት ካለው ጭቆና ለመውጣት መታገል እንዳለበት ተናግረዋል።
በውይይቱ መድረኩ የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራሮችም ተሳትፈዋል።