ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 10 ኮምባይነሮችን ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 10 የግብርና ምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን "ኢትዮ ሊስ" ከተሰኘ የግብርና መሳሪያዎች አቅራቢ ድርጅት ተረከበ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማሪያም እንዳሉት፤ ኮምባይነሮቹ ምርት በደረሰባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ይከፋፈላሉ።

ኮምባይነሮቹ የግብርና ምርት ብክነትን በመቀነስ እገዛ እንደሚኖራቸው ነው የገለጹት።

ኮርፖሬሽኑ በየወሩ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ለአቅራቢ ድርጅቱ በመክፈል በሶስት ዓመታት ውስጥ ክፍያውን ለማጠናቀቅ መስማማቱን ተናግረዋል።

በያዝነው ዓመት 22 ኮምባይነሮችን ለማቅረብ መታቀዱን የጠቆሙት አቶ ክፍሌ፤ “ኮርፖሬሽኑ የግብርና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየሰራ ነው” ብለዋል።

ለአንበጣ፣ ለጸረ-አረምና ሌሎች ኬሚካሎች መርጫ የሚውሉ የድሮን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል በጋራ የሚሰራ ድርጅት እያፈላለገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በሚቀርጻቸው ፕሮጀክቶች 6 ቢሊዮን ብር ገቢ የማግኘት ዕቅድ እንዳለው ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም