ለስኳር ህሙማን የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ አነስተኛ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ለስኳር ህሙማን የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ አነስተኛ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የስኳር ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፤ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ለሕሙማኑ የሚያደርጉት ክትትልና ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን የስኳር ሕሙማን ገለጹ።
የዓለም የስኳር ሕመም ቀን በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ "የስኳር ህመምን በመከላከልና በመቆጣጠር ነርሶች ለውጥ ማምጣት ይችላሉ" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ተከብሯል።
የበዓሉ ተሳታፊና ከ15 ዓመታት በላይ ከስኳር ጋር አብረው መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ኃይሉ ተክሉ "የስኳር ሕመም የቤተሰብ ችግር ብቻ ሳይሆን የአገርም ችግር ነው" ብለዋል።
ከመድኃኒት አቅርቦት በተጨማሪ ኦክስጂን የሚያስፈልጋቸው የስኳር ሕሙማን ቢኖሩም፤ የሚፈልጉትን መድኃኒት እንደ ልብ ማግኘት እንደማይችሉ ገልጸዋል።
አንድ ታካሚ ስድስት ወር የሚጠጋ ቀጠሮ ስለሚሰጠው ተገቢውን የጤና ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ እንደማያስችል ተናግረዋል።
ይህም ለስኳር ህመምተኞች ተገቢው ክትትል እንደማይደረግ ያመላክታል ብለዋል።
የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስራዎች እንደማይሰጡ የገለጸችው ደግሞ ወይዘሪት ሃያት አደራ ነች።
መንግሥት ለሌሎች በሽታዎች የሚሰጠውን ትኩረት ለሕሙማኑ እንዲሰጥ ጠይቃለች።
ህብረተሰቡም ራሱን ከበሽታው ለመጠበቅ ክትትል ማድረግ አለበት ብላለች።
የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱራዛቅ አህመድ በበኩላቸው ማህበሩ ሕሙማን ከማገዝ በተጨማሪ የግንዛቤ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አማካሪ ዶክተር ውብአየሁ ዋለልኝ በአገሪቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቁጥር የስኳር ሕመም በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠ ተናግረዋል።
የልብና የደም ሥር በሽታዎች ከፍተኛውን ሞት በማስከተል ቀዳሚ መሆኑን በመጠቆም።
መንግሥት እስካሁን የስኳር ሕመምን ለመከላከል በ500 ጤና ጣቢያዎች የሚሰጠውን አገልግሎት በአንድ ሺህ ጤና ጣቢያዎች ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት 3 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች የስኳር ሕመም ያለባቸው ሲሆን 9 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በቅድመ ስኳር ሁኔታ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዓለም 406 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር ሕመም ጋር እንደሚኖሩ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።