ለአገር መከላከያ ሠራዊት ክብርና ድጋፍ ለማስተባበር የተቋቋመው ግብረ ኃይል መርሃ ግብሮቹን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር መከላከያ ሠራዊት ክብርና ድጋፍ ለማስተባበር የተቋቋመው ግብረ ኃይል መርሃ ግብሮቹን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2013 (ኢዜአ) ለአገር መከላከያ ሠራዊት ክብርና ድጋፍ ለማስተባበር የተቋቋመው የ"ጥበብ ለአገር ክብር" የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ግብረ ኃይል የሚከውናቸውን መርሐ ግብሮች ይፋ አደረገ።
በመጪው ማክሰኞ ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም በመላ አገሪቷ የሚከወነው "ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ" የተሰኘው መርሐ ግብር አንዱ ነው።
በቅርቡ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመው "ጥበብ ለአገር ክብር" የተሰኘው የኪነጥበብ ባለሙያዎች ግብረ ኃይል አባላት በመርሐ ግብራቱ ዝርዝር ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ከግብረ ሃይሉ አባላት መካከል ከያኒ አርቲስት ደበበ እሸቱ "በታሪክ ኢትዮጵያን የወረሩ ጠላቶች ያልፈጸሙት አሳፋሪ ድርጊት ተፈጽሟል" ብሏል።
ይህ "የእናትን ማድጋ የመስበር ድርጊት እንዳይደገም ለመጪው ትውልድ የሚዘክሩ ስራዎችን መስራት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ግዴታችን ነው" ሲልም ተናግሯል።
የሙዚቃ ባለሙያው ዳዊት ይፍሩ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጅማሮ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንደነበረ አስታውሷል።
የክብር ዘበኛ፣ የምድር ጦርና የፖሊስ ሠራዊቶች ሙዚቃና ሙዚቀኛው ክብር እንዲያገኝ ማስቻላቸውን፣ የኢትዮጵያ ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎችን ማፍራታቸውን፣ በሙዚቃው ዘርፍም ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን ማበርከታቸውን ዘርዝሯል።
መከላከያ ሠራዊት ለኪነ ጥበብ ዘርፍ መዳበር ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልጾ ከሰሞኑ አገር በሚጠብቀው ሠራዊት ላይ የተፈጸመው አሳፋሪ ድርጊት የኪነ ጥበብ ሙያተኞችን ማሳዘኑን ተናግሯል።
የኪነ ጥበብ ሰዎች ከሠራዊቱ ጋር በግንባር በመዝመት አኩሪ ስራዎችን እንደሰሩት ሁሉ አሁንም በጥበብ ሙያቸው ለመከላከያ ሠራዊቱ ያላቸውን ክብርና ድጋፍ በተግባር ይገልጻሉ ነው ያለው።
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አርቲስት ተስፋዬ ማሞ ግብረ ሃይሉ በወቅታዊ ክስተትና በአገር ዘላቂ ሠላም፣ ወንድማማችነትና ዕድገት የጋራ እሴቶችን ለማጉላት የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶችን ነድፏል ብሏል።
ዕቅዶቹም በመከላከያ ሠራዊት ተጋድሎ ላይ የተመሰረቱ ሁነቶች ላይ በመመስረት የክውን ጥበባት፣ የሚዲያ ዝግጅቶችና ሕዝባዊ ድጋፍ የማሰባሰብ መርሃ ግብሮች እንደሚከወኑ ይፋ አድርጓል።
ግብረ ሃይሉ በአጭር ጊዜ የሚከወኑ አራት መርሃ ግብሮችን ይፋ ያደረገ ሲሆን እነሱም 'ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ"፣ "የአገር ክብር ሰው አልባ የሙዚቃ ኮንሰርት"፣ 'የአገር ክብር አስራት' እና 'የአገር ክብር ማዕድ' ናቸው።
'ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ' ማክሰኞ ሕዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል፤ ሰው አልባ የሙዚቃ ኮንሰርት ደግሞ ሕዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሠራዊት ዋና ጽህፈት ቤት በሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ታዋቂ ድምጻዊያንን ያካተተ የሙዚቃ ኮንሰርት ይከናወናል።
'የአገር ክብር አስራት' መርሃ ግብር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ታዋቂ ሰዎች በአንገታቸው ሙዳይ በመያዝ ከሕዝብና ከተለያዩ ተቋማት ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሚሆን ድጋፍ የሚያሰባስቡበት ዝግጅት ነው።
'የአገር ክብር ማዕድ'ም ነጻ በወጡ የውጊያ ቀጠናዎች በመገኘት ከሠራዊቱ፣ ከትግራይ ሕዝብና ተገደው ወደ ጦርነት ገብተው እጃቸውን ከሰጡ ወገኖች ጋር ኢትዮጵያዊነትን የሚያፀና የማዕድ መጋራት መርሃ ግብር መሆኑን አርቲስት ተስፋዬ ገልጿል።
ከያኒ ታምሩ ብርሃኑ ከሶስት ቀናት በኋላ "ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በኢትዮጵያዊያን ስለሚከወነው መርሃ ግብር አብራርቷል።
ማክሰኞ ከረፋዱ 5፡00 ሠዓት ጀምሮ በመገናኛ ብዙሃን ዝግጅቱን በማሟሟቅ 5 ሠዓት ተኩል በሁሉም ክልሎች ሁሉም ዜጋ በያለበት ከቤቱ ደጃፍ በመውጣት ለአንድ ደቂቃ ቀኝ እጁን በግራ ደረቱ ላይ በማንበር ለአገር መከላከያ ሠራዊት ክብር ይሰጣል።
በመቀጠልም ለተጨማሪ አንድ ደቂቃ በጭብጨባ ክብሩን ይገልጻል፤ አሽከርካሪዎች በመኪኖቻቸው ጡሩምባ፣ ሕዝቡም በድምፅ ማጉያዎች ለሠራዊቱ ያለውን ድጋፍ ይገልጻል ብሏል።
በዕለቱ የአገር መሪዎች በአንድነት ፓርክ ሆነው በመርሃ ግብሩ የሚሳተፉ ሲሆን በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሚገኙበት የማርች ባንድ ዝግጅቶች ይካሄዳሉ።
ከአንድ ደቂቃ ክብር የመስጠት ሁነት በኋላም 'ኢትዮጵያ' የተሰኘው የድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ እንደሚሰማ፤ ለዚህም መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።