በሩብ አመቱ በአገር ውስጥ የዜጎች የስራ እድል ፈጠራና የስራ ስምሪት ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በሩብ አመቱ በአገር ውስጥ የዜጎች የስራ እድል ፈጠራና የስራ ስምሪት ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5/2013 (ኢዜአ) በበጀት አመቱ ሶሰት ወራት የዜጎች የስራ እድል ፈጠራና የስራ ስምሪት አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስቴርን የበጀት ዓመቱን አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሩብ ዓመቱ ዜጎችን በአገር ውስጥ ስራ ላይ ለማሰማራት ታቅዶ ከነበረው አንፃር አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
በበጀት አመቱ ሶስት ወራት 534 ሺህ 634 ዜጎችን ስራ ለማስያዝ ቢታቀድም ማከናወን የተቻለው 177 ሺህ 736 በመሆኑ ይህም ክንውን ከእቅዱ 31 በመቶ ብቻ ነው ያሉት።
ሚኒስትሯ በሰጡት ማብራሪያ ከስራ ስምሪት አገልግሎት አንፃር መረጃ መዝግቦ በማደራጀት በኩል ከእቅዱ በላይ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
የአገር ውስጥ ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ህግን ተከትለው መስራታቸውን በሚመለከትም በሩብ አመቱ በ178ቱ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ታቅዶ በ148ቱ ላይ የቁጥጥር ስራ መከናወኑ ተገልጿል።
የኤጀንሲዎቹን ፈቃድ አሰጣጥ፣ እድሳትና ቁጥጥርን በተመለከተም ሚኒስቴሩ ከፌዴራል ፖሊስ እና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የስራ ላይ ደህንንት ቁጥጥርን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።
የውጭ አገር የስራ ስምሪት በኮቪድ 19 ምክንያት ቢቀዛቀዝም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመግታትና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ አገር ውስጥ በመመለስ በኩል የተሳካ ስራ መከናወኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የኮቪድ መከላከል ፕሮቶኮል በማዘጋጀት በርካታ ስራዎች እንዳይቆሙና ሰራተኞች እንዳይበተኑ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ፤ ሚኒስቴሩ በሩብ አመቱ በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑ አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ ከግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲ ጋር በተገናኘ ተስፋ የሚሰጡ ተግባራት መከናወናቸውን በመልካም ጎን አንስተውታል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና በትብብር መስራት መቻሉም ጥሩ ጅምር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኮቪድን መከሰት ተከትሎ ማህበረሰቡን በማነቃቃት የተከናወነው መረዳዳትና መተጋገዝም መልካም ተሞክሮ መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
ከእቅድ አንፃር አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴሩ በቀጣይ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
የሰራተኞች መደራጀትን በሚመለከት ግንዛቤ በመፍጠር ሂደት እንዲሁም ዝቅተኛ የጉልበት ክፍያን በተመለከተ ባለፈው አመት የወጣውን አዋጅ ወደ ስራ በማስገባት በኩል መዘግየቱ በድክመት ተነስቷል።