ቀጥታ፡

የተጀመረው እርምጃ የትግራይን ህዝብ ነፃነት የሚያጎናጽፍ መሆኑን በደሴ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ

ደሴ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) የጨካኙ ህወሓት ቡድን መውደቅ ለትግራይ ህዝብ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚደግፉ በደሴ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ፡፡

በደሴ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማው አስተዳደር ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

ከተወላጆች መካከል አቶ ገብረ ስላሴ ገብረ ህይወት እንዳሉት ከአማራ ክልል ህዝብ ጋር ተዋደውና ተዋልደው ከ40 ዓመታት በላይ ያለምንም ችግር ኖረዋል።

"ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን አቅፎ ከያዘኝ ህዝብ ጋር ለመለየት በተለያየ ጊዜ ጥሪና ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል'' ብለዋል፡፡

ይባስ ብሎ ሰሞኑን ደግሞ ለአፍሪካ ኩራት፤ ጋሻና መከታ በሆነው መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ፣ ዘግናኝና  አንገት ያስደፋ ተግባር በመሆኑ እንደሚያውግዙት ተናግረዋል።

መንግስትም የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ አሸባሪውን ቡድን በአጭር ጊዜ ለህግ ማቅርብ እንዳለበት ጠቁመው፤ እርምጃውን በመደገፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ንጹሃን የትግራይ ህዝብ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

 ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ጊዳና ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የስልጣን ጥመኛው አምባ ገነኑ ህወሓት ከወንድማችን የኤርትራ ህዝብ ጋር አጋጭቶ የልጆቻችን ቁስል ሳይደርቅ ሌላ ጥፋት እየፈጸመብን ነው ብለዋል፡፡

የመንግስትንና የህዘቡን ትብብር ያናደደው ህወሓት ተጨማሪ ጥፋት ሳያደርስ ለህግ እንዲቀርብ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙም  ገልጸዋል፡፡

ይህ አረመኔ ቡድን የትግራይን ህዝብ አይወክልም ያሉት ወይዘሮ ጊዳና የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንኑ ተረድቶ የትግራይን ህዝብ ከጭንቅና ከመከራ ለመታደገ የየድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ ጥቅም  እንዳላገኘ ጠቁመው፤ ተስፋው አሁን በተጀመረው እርምጃ ጽንፈኛው ቡድኑን ለህግ ቀርቦ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የለውጡ ተጠቃሚ መሆን ነው ብለዋል፡፡

በህወሓት ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ለትግራይ ህዝብ ነፃነትና ፍትህ ለማምጣት በመሆኑ መንግስተ እርምጃውን በተጠና መንገድ ጨካኙን ቡድን የመደምሰስ ስራው አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ደህንነት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሐሰን መሃመድ  ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ለህግ ማቅረብ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ቡድኑ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚፈፅመው ጭፍጨፋና ኢሰብዓዊ ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም መንግስት የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉንም አስረድተዋል፡፡

የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ  ሌላም የሀገሪቱ ህዝቦች  ቡድኑን አጋልጦ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

መንግስት ህወሓትን እንጂ  የትግራይን ህዝብ የመጉዳት ዓላማ እንደለለው ጠቁመው፤ ህዝቡም ፅንፈኛውን ቡድን እንደማይወክል የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጠንቅቆ ይረዳል ብለዋል፡፡

በየትኛውም አካባቢ ያለ ስጋት ከወንድም እህቶቻቸው ጋር መኖር እንዲችሉም መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

በወይይቱ የትግራይ ተወላጆች፤ የከተማዋ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎችም አካላትም ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም