ቀጥታ፡

የህወሀት አጥፊ ቡድን ላይ ለሚወሰደው ህግን የማስከበር ስራ ድጋፋችንን እንሰጣለን…የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴረሽን

ሀዋሳ  ህዳር 4/2012 (ኢዜአ) የህወሀት አጥፊ ጁንታ ቡድን ላይ መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሰፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴረሽን አስታወቀ ።

የፌዴረሽኑ ፕሬዝዳንት ወጣት ሱልጣን ዓሊ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ህወሃት ባለፉት 27 ዓመታት በስልጣን ቆይታ ፍትሐዊነት በሌላቸው አደረጃጀቶችና አሰራሮች ህዝብን ሲያደናግርና ሲጨቁን ቆይቷል።

ይህ ያንገሸገሸው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባካሄደው ትግል ከቦታው መነሳት መቻሉን ተናግሯል።

በህዝብ ትግል የመጣው ለውጥ መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ያሳተፈና በቡድኑ ሲፈጸሙ የነበሩ ሴራዎች ቦታ እንዳይኖራቸው በማድረጉ የክልሉ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን አብራርተዋል። 

የለውጥ ሂደቱ የፈጠረውን በጋራ ማደግና የመልማት የመደመር ዕሳቤን ያልተቀበለው በዝባዥ ቡድን ጥቅሞቹ ስለሚቀሩበት የተለያዩ ችግሮች እንዲከሰቱና ለውጡ እንዲጨናገፍ ሲሰራ መቆየቱን በመግለጫው ገልጿል።

ህወሓት ጥቅምት 24 የሀገር ደጀንና ኩራት በሆነው መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ አስከፊና አሳዛኝ ጥቃት መፈጸሙ ፌዴሬሽኑን እንዳሳዘነው አስታውቋል።

መንግሥት ክፋትና መለያየትን የህይወታቸው መርህ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የህወሃት ጥቂት ቡድኖችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የጀመረው ህግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፌዴሬሽኑ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገልጿል።

ለመከላከያ ሰራዊት ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ ፌዴሬሽኑ በተለያዩ አከባቢዎች አባላቱ የገንዘብና ቁሳቁስ የማሰባሰብ እንዲሁም የደም ልገሳ መርሀ ግብር ማስጀመሩን ፕሬዝዳንቱ ተናግሯል።

“በሀገሪቱ የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ በተፈለገው ልክ ተተግብሮ ውጤታማ እንዲሆን እነዚህን ቡድኖች ማስወገድ ተገቢ ነው” ያለው ወጣት ሱልጣን ለዚህም የሀገሪቱ ወጣቶች ከመንግሥት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም