በኦሮሚያ ክልል የመማር ማስተማር ስራ በመጪው ሰኞ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የመማር ማስተማር ስራ በመጪው ሰኞ ይጀመራል
አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ ህዳር 7/2013 ዓ.ም. እንደሚጀምር የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የመማር ማስተማር ስራውን አስመልክቶ የትምህርት ቢሮው ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ቀደም ሲል ትምህረት ከጀመሩት የስምንተኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በተጨማሪ ሌሎች የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ህዳር 7 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት ለማስጀመር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከዝግጅቶቹ መካከል በክልሉ መንግስትና ህብረተሰቡ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችና ቤተመጽሃፍት መገንባታቸው ይገኙበታል።
የስምንተኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች ቀደም ሲል መማር የጀመሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ45 ከቀናት ቦኋላ ሚኒስትሪ እና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ይወስዳሉ ብለዋል።
በኮሮና ምክንያት ተማሪዎች ወደ ቤታቸው በመመለሳቸው የሚታወቅ መሆኑን አውሰተው ፤ በዚህም ተማሪዎቹ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ጾታዊ ጥቃትና ለስነልቦና ጉዳት መዳረጋቸውን አስረድተዋል።
አሁን አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት ማስጀመር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የተማሪ ምዝገባው በተፈለገ መልኩ እንዳልሄደ የገለጹት ሃላፊው፤ በኦሮሚያ ክልል በትምህርት ዘመኑ ከ11 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ የተመዘገቡት 9 ሚሊዮን 700 ሺህ ተማሪዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ቀሪዎቹ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ለመማር ማስተማሩ ስኬታማነት ቢሮው ለመህምራን ስልጠና መስጠቱንም ዶክተር ቶላ ተናግረዋል።
ተማሪዎችን በመልካም ሥነ- ምግባር ለማነጽ የገዳ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ነው ያሉት ሃላፊው ፤ የገዳ ስርዓቱ የትምህርት ይዘት፤ ሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች የስልጠናው የትኩረት አቅጣጫ ነው ብልዋል።
የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች 20 ሚሊዮን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለመለገስ ቃል ገብተው እስካሁን የተገኘው 2ሚሊዮን 700ሺህ ብቻ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ቶላ፤ የተማሪ ወላጆች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛና ሳኒታይዘር ለልጆቻቸው በማስያዝ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ቦታ ብቻ እንዲሆኑ ያሳሰቡት ዶክተር ቶላ፤ ለዚህም ህብረተሰቡ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።