የስኳር ህመም በህጻናት እና ወጣቶች ላይ እየጨመረ መምጣቱ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የስኳር ህመም በህጻናት እና ወጣቶች ላይ እየጨመረ መምጣቱ ተገለፀ
አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የአይነት አንድ የስኳር ህመም በህጻናት እና ወጣቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የዓለም የስኳር ህመም ቀን "የስኳር ህመምን በመከላከልና በመቆጣጠር ነርሶች ለውጥ ማምጣት ይችላሉ" በሚል መሪ ቃል ለ30ኛ ጊዜ ነገ በጤና ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ይከበራል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰሎሞን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጊ እየሆነ መጥቷል።
"አብዛኛው ሰው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ቅድመ ምርመራ የማድረግ ልምዱ አነስተኛ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡
ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ወገኖች የስኳር መጠናቸውን በሚፈለገው ደረጃ በመቆጣጠር ጤናማ ሆነው እንዲዘልቁ ነርሶች ለሚጫወቱት ከፍተኛ ሚና እውቅና ለመስጠት መሪ ቃሉ መሰየሙንም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል፡፡
በዓሉ የጤና ባለሙያዎች በተለይ ነርሶች የስኳር ህመምን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የሚጫወቱት ሚና ላይ አተኩሮ እንደሚከበር የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ስኳር ህሙማን ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዱራዛቅ አህመድ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት የስኳር ህመም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የሚገኝ፣ ተላላፊ ያልሆነና ከፍተኛ የህመምና የሞት መንስዔ መሆኑንም ዶክተር አብዱራዛቅ ጠቁመዋል፡፡
በዓለም ላይ 516 ሚሊዮን ሰዎች ከህመሙ ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች እንደሚያሳዩና ከነዚህም አብዛኞቹ ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም ያለባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከዓይነት አንድ የስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ ልጆችና ወጣቶች ቁጥርም በዓለም ላይ በሦስት በመቶ እየጨመረ መሆኑን በመግለጫው ተነስቷል፡፡
በኢትዮጵያ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት 3 ነጥብ 2 በመቶ ዜጎች የስኳር ህመም እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን 9 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በቅድመ ስኳር ሁኔታ ውስጥ ያሉ እና ለአይነት ሁለት የስኳር ህመም ተጠቂ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡