ቀጥታ፡

ፖሊስ በአማራ ክልል የሚገኙ የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞችን በብሔር ለይቶ መዝግቧል መባሉ ሀሰት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖሊስ የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቢሮ በመሄድ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ የድርጅቱን ሠራተኞች በብሔር ለይቶ መዝግቧል ተብሎ የተሠራጨው ወሬ ሀሰት መሆኑን የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይሉ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ፣ ነገር ግን የህወሃት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች የሆኑ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ተአማኒ እና ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘቱን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የምርመራ እና የሕግ ማስከበር ሥራውን መቀጠሉን በመግለጫው አመላክቷል።

የአማራ ክልል ፖሊስና ሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የነዚህን ተጠርጣሪዎች ዝርዝር ከድርጅቱ መዝገብ አመሳክረዋል እንጂ ሠራተኞችን በብሔር ለይተው አልመዘገቡም ብሏል።

ፖሊስ የተጠርጣሪዎችን ዝርዝር በማቅረብ በአማራ ክልል በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቢሮ መሥራታቸው እንዲረጋገጥለት ጠይቋል እንጂ የሠራተኞች ዝርዝር በብሔር ተለይቶ እንዲቀርብለት አልጠየቀም።

መንግሥት የሕግ ማስከበር ሂደቱን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በሚከውንበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚከፋፍል እና መሠረተቢስ የሆነ መረጃን ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን ብሏል የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ በላከው መግለጫ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም