"የጥፋት ቡድኑን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ይሰራል" -- ብልጽግና ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
"የጥፋት ቡድኑን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ይሰራል" -- ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) የህወሓትን የጥፋት ቡድን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።
"የነፍሰ በላው ቡድን ፍጻሜ እስኪጠናቀቅ በየአካባቢው ሊፈጥራቸው የሚችለውን እኩይ የጥፋት ሙከራዎች በመረዳት የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላ የሀገራችን ሕዝቦች አካባቢያችሁን በንቃት በመጠበቅና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ" ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
ፓርቲው "አገራችን ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንባት እንጂ የአረመኔዎችና የወንበዴዎች ዋሻ አትሆንም" ሲል መግለጫ አውጥቷል።
"ፓርቲያችን ብልጽግና ይህን የጥፋት ቡድን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማረጋገጥ ይወዳል" ብሏል፡፡
"የባንዳው ቡድን በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈፀመው አሳፋሪ የአገር ክህደት ወንጀል፤ ከበረሃ የጀመረና የትግል ጓዶቻቸውን በመክዳት እያደገ የመጣ የባንዳነት የልምምድ ውጤት ነው" ያለው ፓርቲው "ለእውነተኛ ትግል የወጡ ወንድሞቻቸውን በተኙበት መረሸንና ንጹሃን ታጋዮችን በሴራ ወንጅሎ ማጥፋት እያደገ የመጣ የባንዳነት የልምምድ ውጤት ነው" ሲል ገልጿል።
ከሀዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊትና በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን የጭካኔ ተግባራት መላው ሕዝቦች በሠላማዊ ሰልፎች እያወገዙት እንደሆነም ገልጿል።
የጥፋት ቡድኑ ከሕዝብ በዘረፈው ሀብት እንደ ኦነግ ሸኔ አይነት ጽንፈኛ ቡድኖችን አደራጅቶ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በማንነት ላይ ተመስርቶ ንጹሃን ዜጎችን በጭካኔ ጨፍጭፏል ሲልም አክሏል፡፡
የጥፋት ሀይሉ በተደጋጋሚ ያካሄደው የእጅ አዙር ጭፍጨፋ አገር የማፍረስ እቅዱን ሊያሳካለት ባለመቻሉ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የመጨረሻውን ቀይ መስመር አልፎ በአገር ሉዋላዊነት ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ፈጽሟል ሲል ገልጿል ፡፡
"አረመኔው ቡድን ለሀገራቸው ክብር መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ከጀርባ በመውጋትና ንጹሃንን በመጨፍጨፍ የፈጸማቸው ወንጀሎች የሕዝባችንን ስሜት ፈንቅሎ በቁጣ አደባባይ እንዲወጣ አድርጎታል" ብሏል ፓርቲው፡፡
ሕዝቡ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በሠላማዊ ሰልፎች ከመጠየቅ ባሻገር መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በተለያየ አግባብ እየደገፈ መሆኑንም አስታውቋል።
ከብልጽግና ፓርቲ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ መልዕክት ይህ ነው
ሀገራችን ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት የሚሰፍንባት እንጂ የአረመኔዎችና የወንበዴዎች ዋሻ አትሆንም!!!
ከሀዲው የህወሃት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊታችን እና በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸማቸውን የጭካኔ ተግባራት የሀገራችን ህዝቦች በሠላማዊ ሰልፎች እያወገዙት ይገኛሉ፡፡
መንግስት የጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አሸባሪው የጁንታው መሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ሕዝባችን ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ሴረኛው ቡድን የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል በውል ለማሳወቅ በሠላማዊ ሰልፎች መልዕክቱን አስተላልፏል፤ እያስተላለፈም ይገኛል፡፡
ዛሬ ሕዝባችንን ከዳር ዳር ያስቆጣው የሰው በላው ቡድን የጭካኔ ተግባር ለዓመታት በሕዝባችን ላይ ሲተገብረው የቆየው ጥንስስ ሴራ ነው፡፡
የባንዳው ቡድን በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈፀመው አሳፋሪ የሀገር ክህደት ወንጀል፤ ከበረሃ የጀመረና ለእውነተኛ ትግል የወጡ ወንድሞቻቸውን በተኙበት መረሸንና ንጹሃን ታጋዮችን በሴራ ወንጅሎ ማጥፋት እንዲሁም የትግል ጓዶቻቸውን በመክዳት እያደገ የመጣ የባንዳነት የልምምድ ውጤት ነው፡፡
ይህ የጥፋት ቡድን ከሕዝባችን በዘረፈው ሀብት እንደ ኦነግ ሸኔ አይነት ጽንፈኛ ቡድኖችን አደራጅቶ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በማንነት ላይ ተመስርቶ ንጹሃን ዜጎችን በጭካኔ ጨፍጭፏል፡፡
በእነዚህ ኢ-ሰብአዊ የጥፋት እቅዶች ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው በርካታ ንፁሀን ዜጎች በጅምላ ተገድለዋል፣ ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል፣ ህጻናት ያለአሳዳጊ፣ አዛውንቶች ያለጧሪ ቀርተዋል፡፡
በይበልጥ የሕዝባችንን ቁጣ የቀሰቀሰና ኢትዮጵያን ያቆሰለ ጭፍጨፋ በዋና አጋሩ ኦነግ ሸኔ አማካኝነት በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞኖች ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ የፈጀ ከመሆኑም በላይ ጨቅላ ህጻናትን፣ ነፍሰ ጡር ሴቶችን ሳይቀር ፍጹም ሰብዓዊነት በጎደለው ጭካኔ ገድሏል፡፡
የጥፋት ሀይሉ በተደጋጋሚ በንጹሃን ላይ ያካሄደው የእጅ አዙር ጭፍጨፋ ሀገር የማፍረስ እቅዱን ሊያሳካለት ባለመቻሉ ባሳለፍነው ሳምንት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የመጨረሻውን ቀይ መስመር አልፎ በሀገር ሉዋላዊነት ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ፈጽሟል፡፡
ይህ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የተፈጸመው አሳፋሪው ተግባር መላውን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እጅግ ያስቆጣና የፈፀመው የሽብር ተግባር የለየለት ደም አፍሳሽ ወንበዴ ቡድን እንደሆነ በገሃድ አሳይቷል፡፡
ይሁን እንጂ እንኳን ለእናት ሀገር ከሀዲዎች በጠላት ወራሪዎች ያልተበገረው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የእነዚህን ጡት ነካሽ ጁንታ ቡድኖች እኩይ ተግባር ካመከነ በኋላ ዱካቸውን እየተከታተለ በፍጥነት ወደ መልሶ ማጥቃት ዘመቻ በመሻገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህ የጥፋት ሀይል ለፈጸመው ሰይጣናዊ ተግባር ለፍርድ የማቅረቡን ስራ በንቃት እየሰራ ሲሆን በቅርቡ በድል ያጠናቅቃል፡፡
ከሀዲው የህወሓት ቡድን በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስትም ሀገራቸውን በካዱ ወንጀለኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዷል በመውሰድም ላይ ይገኛል፡፡
ይህ አረመኔ ቡድን ከዚህ ቀደም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በእጅ አዙር ሲፈጽመው የነበረውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ አሁንም በቀጥታ በራሱ የጭካኔ ተግባር ፈጽሞታል፡፡
ለአብነትም የጥፋት ሀይሉ በማይካድራ ከተማ እጅግ ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ በንጹሃን ዜጎቻችን ላይ ፈጽሟል፡፡ ይህ ብዙዎች ያለቁበት የጅምላ ጭፍጨፋ አላማና ግቡ በግልጽ የተለየ ነው፡፡
ጭፍጨፋው ከዚህ በፊት ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማስነሳት በተለያዩ አካባቢዎች ሞክሮት ያልተሳካለት የጥፋት ሴራው አካል መሆኑን የሀገራችን ሕዝቦች በውል ተረድተዋል፡፡
ስለሆነም አረመኔው ቡድን ለሀገራቸው ክብር መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ከጀርባ በመውጋትና ንጹሃንን በመጨፍጨፍ የፈጸማቸው ወንጀሎች የሕዝባችንን ስሜት ፈንቅሎ በቁጣ አደባባይ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡
ሕዝቡ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በሠላማዊ ሰልፎች ከመጠየቁም ባሻገር መንግስት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በተለያየ አግባብ እየደገፈ ይገኛል፡፡
ይህ የሕዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በተለይም የነፍሰ በላው ቡድን ፍጻሜ እስኪጠናቀቅ በየአካባቢው ሊፈጥራቸው የሚችለውን እኩይ የጥፋት ሙከራዎች በመረዳት የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላ የሀገራችን ሕዝቦች አካባቢያችሁን በንቃት በመጠበቅና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፋችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ፓርቲያችን ብልጽግና ይህን የጥፋት ቡድን በአጭር ጊዜ ለፍርድ ለማቅረብ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች እንጂ አትፈርስም!
ሕዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ