በአፍሪካ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ጉባኤ የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ጉባኤ የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) ጉባኤ ኢትዮጵያን የሚመጥን የገጽታ ግንባታ ለማከናወን ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ።
አዲስ አበባ በመጪው ህዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም የአፍሪካ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) ስብሰባን ታስተናግዳለች።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የጉባኤውን ቅድመ ዝግጅትና የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅትን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ "በጉባኤው ከ300 በላይ የአፍሪካ የኦሎምፒክ ስፖርት አመራሮች፣ የሌሎች አህጉራት ኦሊምፒክ ማህበር ተወካዮችና ወደ 50 የሚጠጉ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች" ይገኛሉ ብለዋል።
ኦሊምፒክ ኮሚቴው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የጉባኤውን ተሳታፊዎች ተቀብሎ ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚቴው እድሉን በአግባቡ በመጠቀም የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚሰራ የመዝናኛና የገጽታ ግንባታ ኮሚቴ ማቋቋሙንም ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ "ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን የመስተንግዶና የሁነቶች ኮሚቴ ተቋቁሞ ከወዲሁ ዝግጅቶች እየተደረጉ ናቸው" ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለጉባኤው መሳካት እየሰራ የሚገኘውን ብሔራዊ ኮሚቴ በበላይነት እየመሩ መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የአትሌቶችን ዝግጅት በተመለከተም በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአትሌቲክስና የቴኳንዶ ስፖርተኞች ስምንት ወራት አስቀድመው ስልጠና ጀምረዋል ተብሏል።
ዝግጅቱ የተጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን ውጤታማ እንዲሆን ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ዝግጅት እንዲያደረግ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የገለጸው።
የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤሌያስ ሽኩር በበኩላቸው "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለስፖርቱ በሰጡት ትኩረትና እያበረከቱት ባለው አስተዋፅኦ ለሽልማት መብቃታቸው የአገራችንን ስፖርት ከማነቃቃት ባሻገር ለሌሎች የአፍሪካ መሪዎች አርኣያ ይሆናል" ብለዋል።
የአፍሪካ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ለስፖርት ዕድገት ድጋፍ ላደረጉ መሪዎች እና ታዋቂ ሰዎች የሚሰጠውን ሽልማት ያሸነፉት ዶክተር ዐቢይ በጉባኤ ወቅት ሽልማታቸው ይበረከትላቸዋል ተብሏል።
ይህን ስራቸውን በመገንዝብ የአፍሪካ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ሽልማቱን መስጠቱ እንደ አገር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።
ጉባኤውን ለማዘጋጀት የተገኘውን ዕድል በአግባቡ መጠቀምና በቅንጅት በመስራት የአገሪቱን መልካም ገጽታ መገንባት እንደሚገባም ኮሚሽነር ኤሊያስ አስገንዝበዋል።