አይካ አዲስ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ወደ ሥራ እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
አይካ አዲስ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ወደ ሥራ እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀመጠ
አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) አይካ አዲስ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ወደ ሥራ እንዲመለስ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን የተወጣጡ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ፋብሪካው ያለበትን ሁኔታ ዛሬ በመጎብኘት በቀጣይ ህልውናው ላይ ውይይት አድርገዋል።
በዚህም ፋብሪካው ከሥራ ውጪ የሆነበትን ምክንያት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ አጭር ገለፃ ተደርጓል።
ፋብሪካው ሲቋቋም ለበርካታ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ቢጠበቅም በአስተዳደር እና በተለያዩ ተጨማሪ ምክንያቶች ለ13 ዓመታት ኪሳራ በማስመዝገብ ዕዳ ውስጥ እንደገባ ተመላክቷል።
የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካው የተበደረውን ገንዘብ መመለስ ባለመቻሉና ተበዳሪው ከአገር በመጥፋቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ንብረቱን ወስዶ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ተብራርቷል።
ባንኩም ፋብሪካውን ከተረከበ በኋላ ለተወሰነ ወራት ስራውን ማስቀጠል ቢችልም ፋብሪካው በነበረበት ተደራራቢ ችግር የተነሳ ተዘግቶ እንደቆየ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ባንኩ ከ4 ሺህ 500 በላይ የፋብሪካው ሠራተኞች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ በማሰብ ያለ ሥራ ደመወዝ በመክፈል ላይ መሆኑ ተጠቅሷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ፋብሪካው ያለበትን ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲመለስ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
"ፋብሪካው በአንድ ግቢ ውስጥ ሁሉንም አይነት የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ማምረት ይችላል" ያሉት ሚኒስትሩ፣ አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ መመለስ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ፋብሪካውን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት የፋይናንስ፣ የመለዋወጫ አቅርቦት፣ የአስተዳደርና የሠራተኞችን ችግር መፍታት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።
ፋብሪካው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲመለስ ከባለድርሻ አካላት ተወጣጥቶ የተቋቋመው ኮሚቴ በትኩረት መስራት እንዳለበትም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ኮሚቴው የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት ፋብሪካው በተሟላ መንገድ ወደ ሥራ የሚመለስበትን ተግባር በፍጥነት ማከናወን እንዳለበትም አክለዋል።
አይካ አዲስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እ.ኤ.አ ሰኔ 13 ቀን 2006 የቱርክ ዜግነት ባላቸው ሦስት ባለሀብቶች በአንድ ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ካፒታል የተቋቋመ ድርጅት ነው።