አየር መንገዱ የኮቪድ-19 የሕክምና ቁሳቁስን ለሟጓጓዝ ተጨማሪ የጭነት ቻርተር በረራ ጥያቄዎች እየቀረቡለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ የኮቪድ-19 የሕክምና ቁሳቁስን ለሟጓጓዝ ተጨማሪ የጭነት ቻርተር በረራ ጥያቄዎች እየቀረቡለት ነው
አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮቪድ-19 መከላከያ የሚሆኑ የሕክምና ቁሳቁስን ለሟጓጓዝ ተጨማሪ የጭነት ቻርተር በረራ ጥያቄዎች እየቀረቡለት መሆኑን አስታወቀ።
አየር መንገዱ የጭነት አገልግሎቱን ይበልጥ የሚያሳድጉ እድሎች ከፊቱ እንዳሉም ገልጿል።
በታህሳስ ወር 2013 ዓ.ም በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመጀመሪያ ተጠቂ ሰው ከተገኘ በኋላ ቫይረሱ በዓለም ላይ በፍጥነት በመዛመት ብዙ ሰዎችን አጥቅቷል፤ ሌሎች አያሌ ሰዎችንም ለሞት ዳርጓል።
አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል የጉዞና የእንቅስቃሴ ገደቦችን መጣል አንዱ ሲሆን ይሄም በአየር መንገዶች በአጠቃላይ የአቪዬሽን ዘርፉ ላይ ክፉኛ ጉዳት አድርሷል።
የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበርን (አይኤቲኤ) በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እ.አ.አ በ2020 ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪው 252 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጣ ባወጣው ትንበያ አመልክቷል።
ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ አየር መንገዶች 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡም ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የካርጎና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አባዲ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አየር መንገዱ የሚሰጠውን የመንገደኞች በረራ አገልግሎት በአብዛኛው እንዲያቆም አድርጎት እንደነበረ ያወሳሉ።
የአየር መንገዱ ትርፍ 85 በመቶ ገደማ የሚገኝበት የመንገደኞች በረራ በመሆኑ የበረራዎች መቆም በአየር መንገዱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ "ከእድገት ወደ ሕልውና ማቆየት" በሚል መርህ በጭነት አገልግሎት ላይ ርብርብ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም አየር መንገዱ ካሉት የጭነት አገልግሎት ከሚሰጡ አውሮፕላኖች በተጨማሪ 25 የመንገደኞች ሟጓጓዣ አውሮፕላኖችን መቀመጫ በማንሳት የጭነት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል።
በጭነት አገልግሎቱ በአምስት አህጉራት በሚገኙ ከ80 በላይ አገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሕክምና ቁሳቁስ ማጓጓዙንም ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።
በተጨማሪም ከመደበኛ በረራዎች ውጪ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች በጭነት ቻርተር በረራ የሕክምና ቁሶችን ማጓጓዙን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱ የሕክምና ቁሶችን ሟጓጓዝ መቀጠሉንና ለእዚህም ከ50 እስከ 60 የሚሆን የጭነት ቻርተር በረራ ጥያቄዎች እንደቀረቡለትም አቶ ፍጹም ለኢዜአ ገልጸዋል።
ጥያቄዎቹ የቀረቡት የጭነት አገልግሎት እየሰጠባቸው ከሚገኙ አገራትና ተቋማት እንደሆነም ተናግረዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአየር መንገዱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን በፍጥነት ወደ ጭነት አገልግሎት በማዞር ሊመጣ የነበረውን ጉዳት ከመቋቋም አንጻር የአመራሮች ፈጣን ውሳኔና የሠራተኞች ትጋት ወሳኝ እንደነበረም ተናግረዋል።
"አየር መንገዱ ቱሪዝምን ከማስተዋወቅ ባለፈ የተለያዩ ምርቶችን በሟጓጓዝ የጭነት አገልግሎቱን ይበልጥ የሚያሳድጉ እድሎች ከፊቱ አሉ" ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የጭነት አገልግሎት አስመልክቶ ጋዜጦችና መጽሔቶችን በሚያሳትመው "ኤር ካርጎ ኒውስ" የተባለ አሳታሚ ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2020 ምርጥ የአፍሪካ የጭነት አገልግሎት ሰጪ በሚል ሽልማት መስጠቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የካርጎና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ሠራተኞች ሽልማቱን አስመልክተው ትናንት የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው እነዚህ ሠራተኞች በሽልማቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሽልማቱ በኮቪድ--19 ወረርሽኝ ወቅት ፈተና ቢገጥማቸውም ጠንካራ ስራን በመስራት ላስመዘገቡት ውጤት የተገኘ እውቅና መሆኑን ተናግረዋል።
ሽልማቱ ለቀጣይ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ገልጸው አየር መንገዱ በጭነት አገልግሎት የላቀ ውጤት እንዲስመዘግብ ተግተው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ተስፋዬ ይልማ፣ ፅዮን ረጋሳ እና ገመቺስ ብርሃኑ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዓመቱ 1 ሚሊዮን ቶን የሚጠገ ጭነት እንደሚያጓጉዝ መረጃዎች ያመለክታሉ።