ቀጥታ፡

የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን አገራዊ ክህደት ፈጽሟል - መኢአድ እና ባልዴራስ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4/2013 ( ኢዜአ) የህወሃት ፅንፈኛ ቡድን በሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ተግባር አገራዊ ክህደት ነው ሲሉ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ባልዴራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልዴራስ) ፓርቲ አመራሮች ገለፁ።

የፓርቲዎቹ ሃላፊዎች ወቅታዊና አገራዊ ሁኔታን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የህዝብ ግንኙነት ዶክተር በቃሉ አጥናፉ እንዳሉት ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ታጣቂ ሃይል በሰሜን አዝ ላይ የፈፀመው ድርጊት "ትልቅ አገራዊ ክህደት ነው"።

የዚህ አገራዊ ክህደት ፈፃሚ የሆኑት የህወሃት ቡድንና ኦነግ ሸኔ በሽብርተኝነት መዝገብ ላይ ሰፍረው በወንጀል እንዲጠየቁም ተናግረዋል።

በፅንፈኛው ሃይል ላይ ህግ በማስከበር ስራ ላይ የተሰማራው የአገር መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል እየፈፀሙት ያለው ተግባር የሚያኮራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው የሽብር ቡድኑ የፈፀመውን እኩይ ተግባር በማውገዝ በፀጥታ ማስከበር ስራ ላይ ለተሰማራው የአገር መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ሃይል ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕሬዚደንት ማሙሸት አማረ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ደጀን በሆነው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈፀመው የትም ዓለም የሌለ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የፅንፈኛው ህወሃት ቡድን የፈፀመው "ፍጹም አሳፋሪ፤ አስነዋሪና በህዝብ ልጆች ላይ የተፈጸመ ክህደት" ሲሉም ተናግረዋል።

ፅንፈኛው ሃይል በማይካድራ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀመው ጭካኔ የተሞላበት የጅምላ ግድያም ይቅር ሊባል የማይቻል የአረመኔዎች ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የህወሃት ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊትና በአማራ ልዩ ኃይል እየደረሰበት ባለው ሽንፈት ተስፋ በመቁረጡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎችን ለመግደል ተነሳስቷል ብለዋል።

የአረመኔውን ቡድን ተግባር በመመከት በሰራዊቱ እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር ተግባር እንዳለ ሆኖ ህዝቡም በየአካባቢው እየተደራጀ ራሱን መከላከል እንዳለበት አሳስበዋል።

የህወሃት እና ኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድን በሰራዊቱና በህዝቡ ትብብር ተደምስሶ የኢትዮጵያዊያን የድል ቀን ቅርብ እንደሚሆንም አንጠራጠርም ነው ያሉት አቶ ማሙሸት።

የፓርቲዎቹ አመራሮች መንግስት እያከናወነ ባለው ህግ የማስከበር ተግባር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም ዓቀፍ የሲቪክ ማህበራትና የኃይማኖት ተቋማት ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም