ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ የኃይል ግብይት ማደግ የጎላ ሚና ይኖረዋል-አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሠረት

ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጠናዊ የኃይል ግብይት ማደግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዓለምፀሐይ መሠረት ተናገሩ።

ኢትዮዽያ ከዩጋንዳ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትሰራለች ሲሉም ገልጸዋል።

አምባሳደሯ ከኢንዲፔንደት የዜና ምንጭ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ ስለሚኖራቸው የሁለትዮሽ፤ የንግድና የምጣኔ ሀብት ግንኙነት ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ዓለምፀሐይ ኢትዮጵያና ዩጋንዳ የቆየ ሁለንተናዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ቢሆኑም ነገር ግን ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ታሪካዊና ጠንካራ ግንኙነት እንዲሁም ሀገራቱ ካላቸው ሠፊ ዕድል አኳያ በሚጠበቀው ደረጃ ላይ አይገኝም ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ዘርፎች ግን አበረታች እንቅስቃሴዎች እንዳሉ በመጠቆም።

አምባሳደሯ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር ያለውን ሁኔታ ሲያብራሩ “ውይይቱ በግድቡ መገንባት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም'' ያሉ ሲሆን ዋናው ጉዳይና ሰፊ ውይይት የተካሄደበት ፍትኃዊ የውሀ አጠቃቀም ላይ ነው” ብለዋል።

የግድቡ ግንባታም በስኬት እየተከናወነ ይገኛል፤አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ሥራውም 76 ከመቶ በላይ ደርሷል እንዲሁም የሲቪል፤ኤሌክትሪካልና ሜካኒካል ሥራዎችን ያካትታል ብለዋል።

የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት 4 ነጥብ 9 ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ በስኬት መጠናቀቁ የግድቡ ስኬት ማሳያ ነው ያሉት አምባሳደሯ፤ በዚህም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ብለዋል።

አምባሳደር ዓለምፀሐይ ታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን አርማ ተደርጎ የሚወሰድ ፕሮጀክታችን እንድሆነ አስረድተዋል።

ግዙፉ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ6ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችልና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

ኢትየጵያ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላትና የህዝቧቁጥርም በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝ በዛው ልክም ከኢኮኖሚዋ ዕድገት መጨመር ጋር ተያይዞ ሰፊ የኃይል ፍለጎት ትሻለች ነው ያሉት።

የፕሮጀክቱ ዓብይ ዓላማ ከ 65 ሚሊዮን በላይ የኃይል ዕጥረት ለተጋለጡት ኢትዮጵያዊያን ፍላጎት ከማሟላቱም በላይ ቀጠናዊ የሀይል ትስስር ይፈጥራል ሲሉም አክለዋል አምባሳደር ዓለምፀሐይ ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከኢትዮጵያ ባሻገር ቀጠናዊ ፋይዳውም ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል።

ግድቡ በኃይል ግብይት በሀገራቱ መካከል የትብብር ግንኙነት እና በቀጠናው የሚያጋጥመውን የኃይል ዕጥረት በሰፊው እንደሚቀርፈው አስረድተዋል።

የግድቡ መጠናቀቅም ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት መሠረት ያደረገ በአነስተኛ ክፍያ እንድታቀርብ እንደሚያስችላትም ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ማህበረሰብ በዩጋንዳ የንግድ እንቅስቃሴና የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግብይት ትስስር እንዲጎለብት እያደረጉ ያሉት ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።

በዩጋንዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ፤በትራንስፖርት ፤በግብርና፤ በገቢ ንግድ እንዲሁም ባንክን ጨምሮ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 14 እስከ 16 /2019 በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ 3ኛው የሚኒስትሮች ልዑካን ምክክር በዩጋንዳ ካምፓላ መካሄዱን አስታውሰው በዚህ የጋራ መድረክም በሁለቱ ሀገራት መካከል በቀጣይ ስትራቴጂካዊ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በትብብር መስራት ላይ ያተኮረ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በወተት፣ ጨርቃ ጨርቅ፤ በቆዳና ሌጦ ምግብና ሌሎችም ዘርፎች በትብብር ለመስራት መግባባታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም