ነዋሪዎቹ በ320 ሺህ ብር የተገዙ ሰንጋዎችን ለሠራዊቱ በድጋፍ አበረከቱ - ኢዜአ አማርኛ
ነዋሪዎቹ በ320 ሺህ ብር የተገዙ ሰንጋዎችን ለሠራዊቱ በድጋፍ አበረከቱ
ድሬዳዋ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር የዋሄል ገጠር ክላስተር ነዋሪዎች በ320 ሺህ ብር የገዟቸውን ሰንጋዎችን ለሀገር ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አበረከቱ።
ለሀገር መከላከያ የምስራቅ እዝ ከፍተኛ አመራሮችም ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሰራዊቱ ያለውን ፍቅርና ክብር ያሳየበት መሆኑን አስታውቀዋል።
ነዋሪዎቹ የገዟቸውን ዘጠኝ ሰንጋዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬ አበርክተዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የህወሃት ሀገር አፍራሽ ቡድንን ለህግ ለማቅረብ የጀመረው ዘመቻ በስኬት እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል ።
ሰንጋዎቹን ለመከላከያ ሠራዊት አዛዦች ያስረከቡት የክላስተሩ አስተባባሪ አቶ ሁሶ ሁሴን እንደገለጽት በክላሰተሩ ስር በሚገኙ የዘጠኝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደሮች ለሠራዊቱ ያላቸውን ወገናዊነት ለመግለጽ ድጋፍን አድርገዋል ።
"ወንጀለኛው ቡድን ለፍርድ እስኪቀርብ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡
የነዋሪዎቹ ተወካይ አርሶ አደር መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ለ27 ዓመት ሀገርን ሲያተራምስ የነበረው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ወንጀል መላውን ህዝብ ያሳዘነና ልብ የሰበረ ድርጊት ነው" ብለዋል ።
የሀገር መከታ የሆነው ሠራዊት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጀመረው ዘመቻ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ነዋሪው እስከ ህይወት መስዕዋትነት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
"ሰራዊቱ እያካሄደ ላለው ህግ የማስከበር ዘመቻ እስከ ግንባር በመሄድ የጉልበት ድጋፍ እናደርጋለን" ያሉት ደግሞ የገጠር ክላስተሩ ነዋሪ ወይዘሮ ሀሊማ ዩያ ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ "የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አፀያፊ ተግባር የፈፀመውን አሸባሪ የህውሃት ቡድን ለህግ ለማቅረብ የተጀመረው ዘመቻ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል፡፡
ነዋሪው ለሠራዊቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በተደራጀ አግባብ የአካባቢውን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡
በኢፌድሪ አየር ኃይል የምሥራቅ አየር ምድብ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አበበ ለገሰና የምስራቅ ዕዝ ደረጃ ሶስት ሆስፒታል አዛዥ ተወካይ ኮሎኔል ብርሃኑ ዘውዴ ከነዋሪዎቹ የተበረከተውን የሰንጋ ድጋፍ ተረክበዋል፡፡
ኮሎኔል አበበ ለገሰ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ ያለውን ፍቅርና ክብር አድንቀዋል ።
"ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ደጋፍ ከሠራዊቱ ጎን መሆኑን ያስመሰከረበት ነው" ብለዋል፡፡
ህዝቡ ከዳር እስከ ዳር ለሠራዊቱ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ ከሃዲውን ቡድን በአጭር ጊዜ ለህግ ለማቅረብ የተጀመረው ዘመቻ እንዲፋጠን ሞራልና ስንቅ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
የተበረከተው ስጦታና የነዋሪዎቹ መልዕክቶች ለሠራዊቱ እንደሚላኩ ኮሎኔል አበበ አመላክተዋል።
ከሰሜኑ ዘመቻ ጎን ለጎን የምስራቅ መከላከያ ሠራዊት ከተጎራባች ክልሎች ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጋር በመቀናጀት የቀጠናውን ሰላም በመጠበቅና የአሸባሪዎችን ተላላኪ አካላት በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር እያከናወነ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ኮሎኔል ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው፡፡
በድሬዳዋ አስተዳደር ስር በሚገኙ በሌሎች ሶስት የገጠር ከላስተሮች በነገው ዕለት ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ ተመላክቷል።