በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ የነገሌ፣ ነቀምቴ እና መቱ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ የነገሌ፣ ነቀምቴ እና መቱ ነዋሪዎች ገለጹ
ነገሌ/ነቀምቴ /መቱ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) መንግስት በህወሓት የጥፋት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በድል እስኪጠናቀቅ ለመከላከያ ሰራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የነገሌ፣ ነቀምቴ እና መቱ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍና የጥፋት ቡድኑን የሚያወግዝ ሠልፍ ዛሬ በየከተሞቻቸው አካሄደዋል።
ከነገሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታሪኩ ወዬሳ በህወሓት የጥፋት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ጥቃት በታሪክ ይቅር የማይባል ነው ብለዋል፡፡
ህወሓት የአፋኝ፣ ገዳይና የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሆኑን በተላላኪዎቹ አማካኝነት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንጽሀንን በመጨፍጨፍና በማስጨፍጨፍ አሁን ደግሞ በትግራይ ተመሳሳይ የጥፋት ድርጊት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።
ቡድኑ በህዝብ ስም እየማለ የሚፈጽመውን የሽብር ተግባር ለማስቆም መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለሠራዊቱ ደጀን በመሆን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
የነገሌ ከተማ ባለሀብት አቶ ግዛቸው ካሳ በበኩላቸው የህወሓትና የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድኖች ተልእኮ እንዳይሳካ መንግስት የጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የሚደግፉ መሆናችውን ገልጸዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪ ሻምበል መኮንን አብደላ በህወሓትና ኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድኖች የሀሰት ፕረፓጋንዳ ሳንዘናጋ አካባቢያችንን ነቅተን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
የጉጂ ዞን ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሬሪ ዋሬ እንደተናገሩት ህወሓት በመከላከያ ሠራዊቱና በንጹሀን ላይ ላደረሰው ጥቃት በህግ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
መንግስት በጥፋት ቡድኖች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሰራ በመሆኑ የህዝብ ተሳትፎና ድጋፍ እንዳይለየው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሰልፍ በመግለጽ ለመከላከያ ሰራዊቱ ሠንጋዎችን አበርክተዋል፡፡
በተመሳሳይ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ህወሓት በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃትና የሀገር ክህደት ወንጀል አጥብቀው እንደሚያወግዙም በሠላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል።
ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ መልካሙ ታደሰ በሰጡት አስተያየት መንግሥት ሕግን ለማስከበር በሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ከጎኑ እንደሚቆሙም አስታውቀዋል፡፡
አቶ ጎበና ገመቹ በበኩላቸው መንግሥት የህወሓትን የጥፋት ድርጊት በማውገዝ ሥርዓት ለማሲያዝ በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።
የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስጌን የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል እንዲጠናቀቅ የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ድርጅቶች አስተባባሪ ዶክተር ዓለሙ ስሜ በበኩላቸው ህወሓተ የሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በአግባቡ እንዳይተገበር የሽብር ድርጊት ሲፈጽም የነበረው ደባ ሳይበቃው በመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የሀገር ክህደት ወንጀል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች መንግሥት የህወሓትን የጥፋት ቡድን ሥርዓት ለማሲያዝ የጀመረውን ህግ የማስከበር ሥራ ፈጥኖ በስኬት እንዲያበቃ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመቱ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዛሬ ባካሄዱት ሠልፍ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት በሀገር ደህንነት ላይ የተፈፀመ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን በመግለጽ አውግዘዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል በከተማዋ የቆሎ ኮርማ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ትዕዛዙ ኑራ ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ዋነኛ ዓላማ ሀገር የማፈራረስ ፍላጎት በመሆኑ በፅኑ እንደሚቃወመው ገልጿል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጥፋት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃ በመደገፍ የበኩሉን እንደሚወጣም አስታውቋል።
ጽንፈኛው የህወሐት ቡድን የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ በነበረው የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ድንገተኛ ጥቃት በህዝብና ሀገር ላይ የተፈፀመ ክህደት ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የሠልፉ ተሳታፊ አቶ በላይ ተሾመ ናቸው።
የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሀኑ ጀምበሬ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃ በመደገፍ ህብረተሰቡ እያሳየ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የፅንፈኛውን ቡድን ተላላኪዎች ነቅቶ በመጠበቅ ሁሉም የአካባቢውን ሰላም እንዲያስከበርም አሳስበዋል።
በሶስቱም ከተሞች ነዋሪዎቹ አደባባይ በመውጣት ባካሄዱት ሠልፍ ላይ ከሰማቸው መፈክሮች መካከል በፅንፈኛው የህወሐት ቡድን ሴራ የኢትዮጵያ አንድነት አይናጋም፣ የሉአላዊነታችን ጋሻና መከታ የሆነው ጀግና መከለከያ ሠራዊታችን በሙሉ አቅማችን ከጎኑ እንቆማለን፣ የህዝባችንን አንድነት በማጠናከር የህወሓትና የኦነግ ሸኔ አፍራሽ ሴራን እናጋልጣለን የሚሉ ይገኙበታል።