ቀጥታ፡

መንግስት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕግን የተከተለና የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ያማከለ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 4/2013 (ኢዜአ) መንግስት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕግን የተከተለና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ፍላጎት ያማከለ እንደሆነ ተነገረ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንት መደበኛ ስብሰባው 38 የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወቃል።

ግለሰቦቹ ከፍተኛ የአገር ክህደት በመፈጸም፣ በሕገ-መንግስትና በሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ በሚፈጸም ወንጀል፣ የጦር መሳሪያ ይዞ በማመፅ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በመጉዳት፣ በሽብርና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ናቸው።

የሕግ ባለሙያዋ መሰረት አያሌው ፖሊስም ሆነ አቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብት ያላቸውን ሰዎች በወንጀል ሲጠረጥሩ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ይቸገራሉ ይላሉ።

ይሁንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል አመራሮች በተጠረጠሩበት ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ ያለመከሰስ መብታቸውን ማንሳቱ ግለሰቦቹን በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

"የመንግስት ቀዳሚ ስራና ሃላፊነት የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው" ያሉት የሕግ ባለሙያዋ በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሕግ ጥሰቶች በመፈፀማቸው ሕዝቡ በመንግስት ላይ ያለው እምነት መሸርሸሩን አስታውሰዋል።

መንግስት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ይከሰቱ ለነበሩ የንጹሃን ዜጎች ሞትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እጃቸው አለበት የተባሉ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ መልካም ጅማሮ ነው ብለዋል።

የሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 54 ቁጥር 5 የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት እንዳላቸው ያስቀምጣል።

በዚያው አንቀጽ ቁጥር 6 ላይ ደግሞ የምክር ቤት አባላት ሆነው እጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲሰሩ ከታዩ የመከሰስ መብታቸውን እንደሚያጡ ተደንግጓል።

በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር መምሪያ ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ደገፉ በምክር ቤቱ ውሳኔ ትክክለኛነት ይስማማሉ።


ጽንፈኛው የህውሃት ቡድን አገር የማተራመሱን ሴራ በአፋጣኝ እንዲያቆም በሕግ ቁጥጥር ስር ሊውል እንደሚገባ ጠቁመው የምክር ቤቱ ውሳኔ ሕግን የተከተለና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ መሆኑን አውስተዋል።

በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረት የዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ አቶ አባይ ጸሃዬ፣ አምባሳደር ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ዶክተር መብራቱ መለስን ጨምሮ 38 የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም