በትግርኛ እና በሲዳሚኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጦች ለንባብ በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በትግርኛ እና በሲዳሚኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጦች ለንባብ በቁ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 4/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በትግርኛ እና በሲዳሚኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ ተጨማሪ ሁለት ጋዜጦችን ለንባብ አብቅቷል።
ድርጅቱ የ80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል የማብሰሪያ ስነ-ስርዓት አካሂዷል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንደገለጹት ከዚህ በፊት ለህትመት ከሚጠቀምባቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ በትግርኛ እና በሲዳምኛ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጦች ለንባብ በቅተዋል።
ዛሬ ለስርጭት የበቁት በትግርኛ ቋንቋ የሚታተመው "ወጋህታ"፣ በሲዳምኛ ቋንቋ የሚታተመው ደግሞ "በካልቻ" የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
"ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የለውጥ ማሻሻያ ተግባራትን እያከናወነ" እንደሚገኝም ነው አቶ ጌትነት የተናገሩት።
ከማሻሻያዎቹ መካከል ተቋሙን በአዲስ መልክ ማደራጀት፣ ማስተዋወቅና ብዝሀነትን ማስተናገድ በዋናነት እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።
"ከዚህ በፊት ያጋጥሙ የነበሩ የመልካም አስተዳደርና መሰል ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ ለማሳካት አዲስ አደረጃጀት አስፈልጓል" ብለዋል።
በቅርቡም በአፋርና እና በሶማሌ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጦችን ለንባብ ለማብቃት ሥራ መጀመሩን ነው አቶ ጌትነት ያስታወቁት።
እንደ እሳቸው ገለጻ ድርጅቱ ላለፉት 80 ዓመታት በየዕለቱ ለአንባቢያን ተደራሽ በመሆን ለቋንቋና ስነ ጹሑፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ወደ ፊትም በነባር ማንነትና በአዲስ ገጽታ ለዓመታት ያካበተውን ልምድ ተጠቅሞ ተነባቢና ተደራሽ የህትመት ሚዲያ ሆኖ ለመቀጠል እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፌደራል ደረጃ በትግርኛ ቋንቋ ጋዜጣ ሲታተም የመጀመሪያ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ነብዩ ስዑል ሚካኤል ናቸው።
ህትመቱ መጀመሩ ለትግራይ ህዝብ ትልቅ ድል መሆኑን የገለጹት አቶ ነብዩ፤ "የትግራይ ህዝብ የታገለው በራሱ ቋንቋ ለመጻፍ፣ ለመናገር እና ሀሳቡን በነጻ ለማንሸራሸር ነው" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ይህ እውን ሆኖ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታመነ ተሰማ በበኩላቸው " የበካልቻ ጋዜጣ ለህትመት መብቃት የሲዳማ ህዝብ የትግል ፍሬ ነው " ብለዋል።
የሲዳማ ህዝብ ከረዥም ዓመታት ትግል በኋላ ይህን ዕድል በማግኘቱ ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የ80 ዓመት ጉዞን የሚያስቃኝ ሙዚየም በቅርቡ ለህዝብ ክፍት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
ድርጅቱ እስከዛሬ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች በሚታተሙ ጋዜጦቹ ለህዝብ ተደራሽ ሲሆን መቆየቱም ተመልክቷል።