ቀጥታ፡

የህወሓት ቡድን በሀሰት ተፈጥሮ፣ በሀሰት ኖሮ ወደ መቃብር እየገባ ያለ ጽንፈኛ ቡድን ነው - የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4/2013 ( ኢዜአ) ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በሀሰት ተፈጥሮ፣ በሀሰት የኖረ፣ ከነተንኮሉ ወደ መቃብር እየገባ ያለ ህገ ወጥ ቡድን ነው ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት ገለጹ፡፡ 

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት እንዳሉት ህገ ወጥ ቡድኑ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት ወገን በወገኑ ላይ ሊያደርገው የማይገባና የአገር ክህደት ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል።    

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ ብርጌድ አዛዥ የነበሩት ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ እንዳሉት ፅንፈኛ ቡድኑ በሠራዊቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት በታሪክ ይቅር የማያስብል ድርጊት ነው፡፡

ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የሚያስጠብቅ የአገር መከታ መሆኑ እየታወቀ እንዲህ አይነት ሴራ እና በደል ሊፈፀምበት አይገባም ነበር ብለዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ የትምህርትና የዘመቻ መኮንን ኮሎኔል ታምሩ ኃይሉ በበኩላቸው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሲጀመር የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሌለው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የጥፋት ቡድኑ በሀሰት ተፈጥሮ በሴራና ተንኮል የኖረና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሌለው በመሆኑ እኩይ አላማውን የተረዱ ሁሉ ጥለውት እንደሄዱ ተናግረዋል፡፡

ከቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት መካከል ሻምበል ነቢያት ከበደ፤ የትግራይ ህዝብ አገር ወዳድና ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በአብሮነትና ፍቅር የኖረና በቀጣይም የሚኖር ለመሆኑ ማንም አይጠራጠርም ነው ያሉት።

ፅንፈኛው የህወሃት ስብስብ ግን ከዚህ የተለየ አላማ አንግቦ የሚሰራ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

ሻምበል ነቢያት ከበደ እና ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ እንዳሉት የህወሃት ቡድን "የእናት ጡት ነካሽ" በመሆኑ በመከላከያ ሃይሉ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በተለያዩ ጊዜያት የእርቅ ሃሳብ ሲቀርብለት አሻፈረኝ ያለው ህገወጥ ቡድን አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ድርድር ማለቱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የአገር መከታ የሆነው የሰሜን እዝ በፅንፈኛው ሃይል ከተመታ በኋላ ከቡድኑ ጋር መንግስት የሚያደርገው ድርድር መኖር እንደሌለበትም ጠቅሰዋል።

የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት መንግስት በማንኛውም ጊዜ ጥሪ ካደረገላቸው ጥሪውን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

አባላቱ የአገር ሉአላዊነትን በማስከበር፣ ዳር ድንበሯን በማስጠበቅና የህዝብ አለኝታ በመሆን አኩሪ ተግባር የፈፀሙ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም