ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በፅንፈኛው የሕወሃት አባላት ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት ያለው ነው... የፖለቲከ ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአገር ክህደትና ሽብርተኝነት ወንጀሎች የተጠረጠሩ የምክር ቤቱ አባላትን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት ያለው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

ፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደህንነት ስጋት በመሆኑ ሕግ ፊት መቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረበለትን የ38 የምክር ቤት አባላት ‘ያለመከሰስ መብት ይነሳልኝ’ ጥያቄ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁ ይታወሳል።

ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ ያደረጉት የብልጽግና፣ የኢዜማና የትዴፓ ፓርቲ አመራሮች ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት ያለው እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ በሽብር፣ በአገር መክዳትና በጦር መሳሪያ ማከማቸት ወንጀል የተሳተፉትን ተጠያቂ ለማድረግ በዐቃቤ ህግ በኩል እርምጃ መጀመሩ ተገቢነት ያለው ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የሕወሃት የጥፋት ቡድን ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ በማንነት የከፋፈለ፣ አገራዊ ተቋማትን ያፈራረሰ፣ አገሪቷን ዘርፎ በውጭ አገራት ሃብት ያከማቸ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም የአገር ሉዓላዊነት በሚያከብር ሰራዊት ላይ የፈጸሙው ጥቃት አገርን የመክዳትና ለጠላት አሳልፎ የመስጠት ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው “ሕወሃት ለ29 ዓመታት ኢትዮጵያ ላይ ያልፈጸመው የጥፋት ድርጊት የለም” ብለዋል።

በምክር ቤቱ ከተጠቀሱ ወንጀሎች በተጨማሪ ሕወሃት ከበረሃ ጀምሮ በድርቅ ለተጎዳው የትግራይ ህዝብ የመጣን ሰብዓዊ እርዳታ በመንጠቅ ህዝቡን በረሃብ በመግደል የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸመ ድርጅት መሆኑንም ገልጸዋል።

መቀሌ ከመሸገም በኋላ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ ከልሎች የሽብር ቡድኖችን እየጠራ ሲያሰለጥን እንደነበር ገልጸዋል።

በየክልሎቹ ለሚፈጠሩ ግጭቶችም የሽብር ቡድኑ እጅ እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም ለረጅም ዘመን ታፍራና ተከብራ የኖረችን አገር መድፈር ለማንም መፈቀድ እንደሌለበት ገልጸዋል።

ሕወሃትን እስካሁን ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ የመንግስት ለዘብተኝበነት እንደነበር ገልጸዋል።

“ቡድኑ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የአንበጣ ወረረሽኝና የታላቁ ህደሴ ግድብ አገራዊ ጉዳዮች ባሉበት ወቅት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ነውር የቤትን አጥር አፍርሶ ለጠላት በር የመክፈት አገራዊ ክህደት ነው” ብለዋል።

የራሱ ወገን የሆነን የአገር መከላከያ ሰራዊት ከመውጋት በላይ የአገር ክህደት ወንጀል የለም ብለዋል አቶ የሺዋስ።

ቡድኑ ስልጣን ላይ ሆኖ ያወጣውን ህገ መንግስት በተጻረረ መንገድ የፌዴራል ተቋማትን ለማፍረስ ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀው፤ ህግን የማስከበር እርምጃዎች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፅንፈኛው ቡድን ከኢትየጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ደህንንት ስጋት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ለህግ መቅረብ እንዳለበትም ገልጸዋል።

ምክር ቤቱም የሽብር፣ የአገር ክህደትና የመሳሪያ ማከማቸት ወንጀሎች የተጠረጠሩ የጽንፈኛው የህወሃት አባላት ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ቢዘገይም ተገቢነት ያለው መሆኑን የፓርቲዎቹ አመራሮች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም