ቀጥታ፡

በጉሊሶ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው

ነቀምቴ፣ ህዳር 03/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ግርማዬ ዳባ እንዳሉት በወረዳው በጋዋ ጋንቃ ቀበሌ በታጠቁ ኃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 1ሺህ 44 ቤተሰብ ያላቸው 267 አባወራዎች ይገኛሉ፡፡

ተፈናቃዮቹ በወረዳው  ተጠልለው በሚገኙበት አካባቢ  እስካሁን ከወረዳው የመጠባበቂያ ፈንድ ከ94 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።

የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት በበኩሉ  ስንዴ፣ የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ የተለያዩ የቤት መገልገያ ቁሳቁሶችና አልባሳት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም  100 ሺህ ብር  በሆነ ወጪ ምግብ ነክ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ግዥ እየተካሄደ  ነው ብለዋል፡፡

ከኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም  192 ፍራሾችና ብርድ ልብሶች፣ 183 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት፣ 540 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 61 ኩንታል ማካሮኒ፣ 322 ካርቶን ፓስታና ሌሎች  ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አቶ ግርማዬ  ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ   ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዞኑ የአስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቢዩ ምህረቱ በበኩላቸው የፀጥታ ኃይል በቦታው በመመደቡ በአሁኑ ጊዜ ምንም የጸጥታ ሥጋት የለም ብለዋል፡፡

በቂ የፀጥታ ኃይል ተመድቦ አካባቢውን እየተቆጣጠረ በመሆኑ የፀጥታ ችግር እንደሌለ የገለጹት ደግሞ  የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤሊያስ ኡመታ  ናቸው፡፡

አቶ ኤሊያስ ተፈናቃዮቹ ተጠልለው ያሉት ከነበሩበት አካባቢ ብዙም ርቀት ስለሌለው ወደ እርሻው ቦታቸው ሄደው የደረሰ ሰብላቸውን እየሰበሰቡ ነው ብለዋል፡፡

ከተፈናቃዮቹ መካከል አርሶ አደር ደሣለኝ አሻግሬ በሰጡት አስተያየት ገንዘብና ንብረታቸው ተዘርፎ ለችግር መጋለጣቸውን ገልጸው፤ መንግሥት  የምግብ  ፣ ፍራሽና የብርድ ልብስ ድጋፍ አድርጎልኛል ብለዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር ፋንታሁን ዘመን በበኩላቸው  መኖሪያ ቤታቸው ከነሙሉ ዕቃው እንደተቃጠለባቸው ጠቅሰው፤   የምግብ ችግር እንደሌለባቸውና አካባቢው  እየተጠበቀ በመሆኑ የፀጥታ ችግር የለም ብለዋል፡፡

መንግሥትና የአካባቢው ሕብረተሰብ  ምግብ፣ ብርድ ልብስና ፍራሽ  ድጋፍ እንዳደረገላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው ተጎጂ  አርሶ አደር ሸጋው ከተማ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም