የህወሓት ቡድን ተጨማሪ የጥፋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም -አሰተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓት ቡድን ተጨማሪ የጥፋት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም -አሰተያየት ሰጪዎች
አዳማ፣ ህዳር 03/2013(ኢዜአ) የህወሓት ቡድን የያዘው ሃይልና ገንዘብ ሲመናመን ሠላም ፈላጊ መምሰሉ ማመንም ሆነ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ተናገሩ።
ምክር ቤቱ በአዲሱ የበጀት ቀመር ዙሪያ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የምክክር መደረክ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት ባለድርሻ አካላት መካከል የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በተለይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግስትም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ድርድር አይቀበሉም ብለዋል።
ወንበዴው የህዋሃት ቡድን የያዘው ሃይልና ገንዘብ ሲመናመን ለተጨማሪ ጥፋት ጊዜ መግዣ ሰላም ፈላጊ መምሰሉ እንደማይታመን ገልጸዋል።
አሁን ሀገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ህግን የማስከበር ሂደት በጣም ተገቢ ነው፤ በተለይም ዘራፊው ቡድን አንድ ማዕከል ላይ በመመሸግ ሀገሪቱን ለማፍረስ ያሰበውን እቅድ በማክሸፍ ረገድ ኦፕሬሽኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ከቡድኑ ጋር ለመደራደርና ለመስማማት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች ጭምር መንግስት ሰፊ ጊዜ ሰጥቷቸው በትዕግስት ሲጠብቃቸው እንደነበር አሰታውሰዋል።
ህዝቡም በሀገሪቱ በየቦታው በሚከሰተው ግጭት፣ መፈናቀልና ሞት እንዲቆም መንግስት የህግ የበላይነት እንዲያስከብር ሲጠይቅ እንደነበርም አመላክተዋል።
መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ለድርድር የማይቀርብ ከመሆኑም ባለፈ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሲባል መሆኑንም ተናግረዋል።
በድርድር ስም መዘናጋት አይገባም፤ የውጭ ጫናም አንቀበልም፤ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው ብለዋል።
ከቢሮው ሠራተኞች ጋር ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ ከስምምነት ደርስናል ሲሉም ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በክልላቸው የሞግዚት አስተዳደርና አሰራር ሲያስፈፅም የነበረው ህወሐት ከነበረው አስተሳሰብ ያለመላቀቁ አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡበንግ ኡቶው ናቸው።
ቡድኑንና ተላላኪዎቹን ለህግ ማቅረብና ላጠፉት ጥፋት ተጠያቂ ማድረግ አለበት ያሉት ሃላፊው፤ ሀገር በግለሰቦችና ቡድን እንዳትፈርስ ወንጀለኞች ከያሉበት ተፈልገው ለህግ መቅረብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
አሁን በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ እያንዳንዱ ሰው አካባቢውን እንዲጠብቅ ብሎም ችግር ፈጣሪዎችን ለፀጥታ አካላት እንዲያሳውቁ እየሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተጨማሪም እንደ ክልል የልማት ስራዎችን እየሰራን የሚጠየቀውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
እየተካሄደ ያለው ኦፕሬሽን ጦርነት ሳይሆን ህግ የማስከበር ነው፣ ህወሓት ከባህሪው የተነሳ ሲፈፅም የነበረው ድርጊት ጦርነት እንዲነሳና ሀገር እንዲበተን ይፈልጋል ያሉት ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል አቶ ተረፈ በዳዳ ናቸው።
የትግራይ ህዝብ የሀገር አንድነት እንዲቀጥል ከመንግስትና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም እንዳለበትም አመልክተዋል።
ህዝቡ ይሄን አፍራሽና ጨቋኝ ሃይል ከጫንቃው በማስወገድ የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ አስተያየት ሰጪዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።