ቀጥታ፡

ሱዳናውያን ህግ የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ላይ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ደም ለገሱ

መተማ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) ''የአፍሪካ ኩራት ለሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እኛም ከጎኑ መሆናችንን ደም በመለገስ እናረጋግጣለን'' ሲሉ ሱዳናውያን ዛሬ በመተማ ዮሐንስ ከተማ ደም በመለገስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት ያወገዙት ሱዳናዊያኑ የሀገሪቱ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃም እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

ደም ከለገሱት መካከልም በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የጋላባት ከተማ ነዋሪው ወጣት አብዱላዚዝ ሀሰን እንደተናገረው፤ በሰራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት የሚያሳፍርና ይቅር የማይባል ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃም እንደ ጎረቤት ሀገር ዜጋ እንደሚደግፈው ተናግሯል።

''ሱዳንና ኢትዮጵያ ካላቸው የንግድና የፖለቲካ ትስስር ባሻገር ጥብቅ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አላቸው'' ያለው ደግሞ ሌላኛው የዚሁ ግዛት ነዋሪ ማህሙድ አልአባዲ ነው።

የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለሱዳን ሰላም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፆ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአካባቢው ሰላም መስፈን ላደረገው እገዛ ደም በመለገስ ድጋፉን ማሳየቱን ገልጿል።

የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ አዲሱ በበኩላቸው “ዛሬ ሱዳናዊያኑ ያደረጉት የደም ልገሳ ፕሮግራም የሁለቱ ሀገሮች ዜጎችና መንግስታት ያላቸውን ጥብቅ የሆነ ግንኝኑነት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

''በኩታ ገጠም አስተዳደር በጋራ በመሆን ህግ ለማስከበርና አካባቢያዊ ደህንነትን ለመጠበቅ አብረን እየሰራን ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።

አሁን መንግስት እየወሰደ ባለው ህግ የማስከበር እርምጃም ወንጀለኞች እንዳያመልጡ ድንበርን በመዝጋት የሱዳን መንግስት ያደረገው አስተዋጽኦም ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን አቋም ያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት የበለጠ በሚያጠናክሩ ስራዎች በጋራ እንደሚሰሩ አርጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም