ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ጅማ፣ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ድጋፍ የሚውል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ዛሬ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ እንደገለጹት ከገንዘቡ በተጨማሪ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ጀምረዋል፡፡
የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞቹ ያደረጉት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለመከላከያ ኃይል ያላቸውን አጋርነት ለማሳየትና አጥፊው ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥርዓት እንዲይዝ የሚደረገውን ትግል ለማገዝ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ቀነኒሳ ለሚ በበኩላቸው የተቋሙ ሰራተኞች ከሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ ቀንሰው ከመስጠት አልፈው ደም መለገስና ሌላም ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውን አስረድተዋል፡፡
መንግስት ተገዶ የገባበት ጦርነት በመሆኑ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ሆነው በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ከድር ኢብራሂም ናቸው።
የመከላከያ ሠራዊቱ እየተዋጋ የሚገኘው ከጨካኙ ጥቂት የህወሐት ቡድን ጋር በመሆኑ ብዙሃኑ የትግራይ ወገኖች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አመልክተዋል።
ዶክተር ገብረ ጻዲቅ ቦሰን በበኩላቸው የሀገር አድን ጥሪውን ተቀብለው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
"ድጋፍ ለማድረግ የወሰንኩት የህወሐት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወደ ኋላ የማይል የክፉዎች ክፉ ስብስብ መሆኑን ስለማምን ነው" ብለዋል፡፡
የጅማ ከተማ ባለሃብት፣ ማህበራትና ሌሎች ነዋሪዎች በትናንትናው ዕለት 4 ሚሊዮን ብርና ምግብ ነክ ቁሳቁስ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጅማ እና ቡኖ በደሌ ዞኖች በሚገኙ ከተሞች ነዋሪዎች ወደ አደባባይ በመውጣት የህወሓትን ክፉ ድርጊት በማውገዝ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን ድጋፍ ገልጿል።