ቀጥታ፡

ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ተግባር ችግሩ በድርድር እንዲፈታ እድል የሚሰጥ አደለም-- አስተያየት ሰጪዎች

አዳማ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ)  ህወሐት በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ተግባር በድርድር ችግሩ እንዲፈታ እድልም ሆነ አማራጭ የማይሰጥ መሆኑን በአዳማ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

መንግስት እስከ መጨረሻው ድረስ ሄዶ የጥፋት ቡድኑን በመደምሰስ ሀገሪቱን  ነፃ ማውጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።

በከተማዋ የደጋጋ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወሰኔ ሳህሌ  ህወሐት የፈፀመው ተግባር ከሀገራችን ባህል ያፈነገጠና በታሪካችን ሰምተን የማናቀው አሳፋሪ ድርጊት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ተዘናጋ እንጂ ህወሃት ለ27 ዓመታት በወንበዴነት ስራ ተሰማርቶ ሲሰራ መቆየቱንም አወስተዋል።

መንግስትም የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ተዋቂ ግለሰቦች ጭምር በመላክ ለድርድርና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሁለት ዓመት ሙሉ ሲለምናቸው ነበር ብለዋል።

አሁን ግን ህወሃት በጥፋት ቡድኑ የፈፀመው ተግባር ችግሩ በድርድር እንዲፈታ እድልም ሆነ አማራጭ የማይሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ወታደሮቻችንን  ገድለው ሬሳቸው  በአውሬና አሞራ እንዲበላ ያደረጉ ጁንታ በመሆናቸው  በህግ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪም ይጠያቃሉ ብለዋል።

ህወሃት መውጫና መግቢያ ሲያጣ፣ መሸነፉን ሲያውቅ ለጊዜ መግዣ እንዲሆነው ነው እንደራደር የሚል ማታለያ ያቀረበው ያለው ደግሞ የጎሮ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አሸናፊ ባልቻ ነው።

ከዚህ በፊት ለረዥም ጊዜ በተሰጣቸው የሰላም ጥሪ ጊዜና አማራጭን በእምብተኝነት መጠቀም አልቻሉም ያለው ወጣቱ፤ አሁን የመፈልገው ለዳግም ጥፋት መፈፀሚያ ጊዜ መግዣ መሆኑን መንግስት መገንዘብ እንደሚገባው ተናግረዋል።

ድርድርም ሆነ እርቅ ከእንግዲህ ከወንበዴው ቡድን ጋር መኖር የለበትም፤  አጥፊውን ቡድን ለህግ አቅርቦ እርምጃ ከተወሰደበትና ሀገር ማዳን ከተቻለ  በኋላ ነው ብለዋል።

ከወጣቶችና ከከተማዋ ህብረተሰብ የሚጠበቀው መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ በጉልበት፣ እውቀትና ገንዘብ መደገፍ  መሆኑን ገልጿል።

በዚህም ሀገር አፍራሽ ቡድን ፈጥኖ ለህግ እንዲቀርብ ወጣቱና ሽማግሌው ጨምሮ መላው ህብረተሰብ በአንድነት ሆኖ ከመንግስት ጎን መቆም አለብን ብለዋል።

ቡድኑ እርቅና ሰላም ቢፈልጉ ሁለት ዓመት ሙሉ በአሻፈረኝ ባልተለመኑ ነበር፤ አሁን የፈለገው  ዳግም በህዝብና በሀገር ለመጫወት ነው ያሉት ደግሞ በከተማዋ የደጋጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መለሰ ስሜ ናቸው።

ስለ ተደረገው ጥቃት የሰማነው መግለጫ የሚያሳዝን ከመሆኑም ባለፈ ቡድኑ ጨካኝና አረመኔ መሆኑን የተረዳንበት ነው፤ ሠራዊቱን ከመግደል አልፎ እስከ ዛሬ ሬሳቸው እንዳይቀበር ያደረገው አረመኔያዊ ድርጊት  ነው ብለዋል።

መንግስት እስከ መጨረሻው ድረስ  ሄዶ የጥፋት ቡድንኑ በመደምሰስ  ኢትዮጵያን ነፃ ማውጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም