ቀጥታ፡

በአጥፊው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ከመንግስት ጎን እንቆማለን - የቀድሞ አየር ወለድ አባላት ማኅበር

ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) የአገር ህልውና ለማስከበር መንግስት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አባላቱ በሙያቸው ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት ማኅበር አስታወቀ፡፡ 

ማኅበሩ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም ከሃዲው የህወሓት ቡድን መከላከያ ሠራዊቱ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ያደረሰበትን ጥቃት አጥብቆ እንደሚቃወመው በመግለፅ ወንጀለኞቹ ለሕግ ሊቀርቡ  ይገባል ባይ ነው፡፡  

የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ኃይለማርያም የሕዝብ ልጅ በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ በጽንፈኛው ቡድን የተፈፀመው ጥቃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ነው ብለዋል፡፡

 ሠራዊቱ የትግራይን ሕዝብ ለ20 ዓመታት የጠበቀና በተለያዩ ጊዜያት ለሚያቀርብለት ጥሪም  በጎ ምላሽ ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጽንፈኛው ቡድን ያደረሰው ጥቃት የአገር ክህደት ተግባር ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት የጀመረውን ሕግ የማስከበርና አጥፊዎችን በፍርድ አደባባይ የማቆም እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

በዚህም የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት ከመንግሥት ጎን ለመቆምና ማንኛውንም ጥሪ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጽንፈኛው ቡድን ቀድሞ ባዘጋጃቸው ቅጥረኞቹ አማካኝነት በተለያዩ ቦታዎች ጥፋት ሊያደርስ ስለሚችል ኅብረተሰቡ አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ወለድ አባላት የአገሪቷን ዳር ድንበር ለማስከበር ደምና አጥንታቸውን የገበሩ መሆናቸው ተናግሯል፡፡

ማኅበሩ በርካታ አባላት ያሉት ሲሆን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎችም ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዳሉት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም