ቀጥታ፡

የቶኪዮ ኦሊምፒክ አትሌቶች መታሰቢያ ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከ56 ዓመታት በፊት በቶኪዮ ኦሊምፒክ ድል ያደረጉ አትሌቶች መታሰቢያ ቀን እያከበረች ነው። 

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1956 ሜልቦርን ጀምሮ በ13 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች  ተሳትፋለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኦሊምፒክ የተሳተፉ አትሌቶች መታሰቢያን ከህዳር 1 ቀን 2013 ጀምሮ እያሰበ መሆኑን አስታውቋል።

መታሰቢያው እስከ ህዳር 13 ድረስ በየዕለቱ በየኦሎምፒኩ የተሳተፉ አትሌቶችን በማስታወስ ይቀጥላል።

በዚህም መሰረት ዛሬ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳታፊ አትሌቶች ቀን እየተከበረ ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ ኦሊምፒክ አምስት ወንድ አትሌቶችን በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ርቀት ውድድሮች እንዲሁም በቢስክሌትና በቦክስ ተሳትፋለች።

ኢትዮጵያን ከወከሉ አትሌቶች አንዱ አበበ ቢቂላ ከአራት ዓመታት በፊት በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግር ሮጦ ካሸነፈ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።

በወቅቱ አበበ ለውድድሩ 40 ቀናት ያህል ሲቀሩት ትርፍ አንጀቱን ቀዶ ጥገና ያደረገበት ስለነበር፤

ውጤት ይዞ ይመለሳል ብሎ ያልጠበቀበት እንደነበርም በታሪክ ተመዝግቧል።

አበበ ግን በኦሊምፒክ ማራቶን ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ኢትዮጵያውያን በደስታ አስፈነደቀ።

በእንግሊዛዊው ባዝል ሔትሌይ በ2ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሴኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1ደቂቃ 43 ሴኮንድ 8 ማይክሮ ሴኮንድ በማሻሻል ክበረ ወሰን በመስበርም ሌላ ታሪክ ሰራ።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ባስመዘገበችው ውጤት ከዓለም 10ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ አንደኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች፡፡

ከድል መልስ በኢትዮጵያውያን የጀግና አቀባበል የተደረገለት አበበ፣ከንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ቮልስ ዋገን መኪና ሽልማትና የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጠው።

ቀናቱ የሚዘከሩት ወጣቱን ትውልድ ለማነቃቃትና ብርታት እንዲሆናቸው በማሰብ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም