ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች እየወሰዱት ላለው ገንቢ እርምጃ አፍሪካ ህብረት አመሰገነ

አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግስታት በመካከላቸው ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር እየወሰዱት ላለው ገንቢ እርምጃ የአፍሪካ ህብረት ምስጋና አቀረበ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በኤርትራ፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂሞ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ለሀገራቱ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ህብረቱ አስታውቋል። "ሀገራቱ በመካከላቸው መተማመንና ትብብር እንዲሁም እርቀ ሠለም እንዲወርድ ላሳዩት ቁርጠኝነት ህብረቱ ምስጋና ያቀርባል" ሲሉ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት ይህ የሰላም ጥረት የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ ከፍተኛ አንቅስቃሴ  እያደረገ ባለበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ሊቀመንበሩ አንስተዋል። የኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊ የሰላም ጥረት በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ የሀገራቱ ተግባር በአጀንዳ 2063 የተጠቀሰውን የአህጉሪቱ ፖሊሲዎች በማስፈጸም ረገድ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ኮሚሽነሩ መናገራቸውን ህብረቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በግጭት ውስጥ ያሉ ሌሎች አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ አስመራ ተጉዘው ኤርትራን ከጎበኙ በኋላ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት አድርገው ሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅሞችን የሚያስከብሩ የተለያዩ ስምምነቶችን አድርገዋል። በስምምነቱ መሰረትም ኤርትራ ከ19 ዓመታት በኋላ ትላንት በአዲስ አበባ ዳግም ኤምባሲዋን ስትከፈት ኢትዮጵያም በአስመራ ኤምባሲዋን እንደምትከፍት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም የሚያስችሏትን ዝግጅቶች እያደረገች መሆኗ ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም