ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም ለአገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 3/2013 (ኢዜአ) "ደማችን ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ስታዲየም ለአገር መከላከያ ሰራዊት የደም ልገሳ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።


የከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮና የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ነው መርሃ ግብሩ።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ደማቸውን ለግሰዋል።


የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በመርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው።


ዛሬ ቀኑን ሙሉ በሚካሄደው መርሃ ግብር ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች ደማቸውን ይለግሳሉ ተብሎም ይጠበቃል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ባለፈ በቀጣይ ቀናት ለመከላከያ ሰራዊቱ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል።


ከተማ አስተዳደሩ ለአገር መከላከያ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችን ትናንት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።


በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራዳ ጊዮርጊስ ቅርንጫፍ፡- 1000354000834 ወይም 1818 የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፡- ኦዳ ቅርንጫፍ 1000048019619፤ አዋሽ ባንክ፡- ፊንፊኔ ቅርንጫፍ 01301854206200 የሂሳብ ቁጥሮች ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።


የአገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል በህወሃት ቡድን ላይ እያከናወነ ላለው የሕግ ማስከበር ስራ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ደም በመለገስ እንዲሁም ገንዘብና ቁሳቁስ በመስጠት ድጋፋቸውን እያደረጉ ይገኛሉ።


ለድጋፉ የሃብት ማሰባሰብ ስራ የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ በሰላም ሚኒስቴር ሰብሳቢነት ትናንት መቋቋሙ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም