ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በሚኒስቴሩ አመራር ላይ የሚታየው ያለመናበብ ችግር እንዲፈታ አሳሰበ

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በተቋሙ የሥራ አመራሮች መካከል ያለውን ተናቦ ያለመስራት ችግር እንዲፈታ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዩ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ የቀረበው የሩብ ዓመት ዕቅድ በርካታ ክፍተቶች ስላለበት ምክር ቤቱ ተከልሶ እንዲመጣም አዟል።

ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴሩን የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ  በእዚህ ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከሚከታተላቸው ተቋማት እንዲሁም ከሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ጋር ተቀራርቦና ተደጋግፎ የመስራት ክፍተት እንዳለበት ተናግረዋል።

" ከሪፖርት አቀራረብ ጀምሮ ተቋማትን የመከታተል ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም " ያሉት ወይዘሮ አበባ፣ ተቋሙ ከተሰጡት ኃላፊነቶች  አንዱ የተለያዩ ተቋማት የሴቶች ፣ ህጻናትንና ወጣቶችን ጉዳይ አካተው እንዲሰሩ ማድረግ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ሚኒስቴሩ በእዚህ ረገድ አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂ በሚያደርግ መልኩ እየሰራ እንዳልሆነ ነው የገለጹት።

"የሩብ ዓመት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ባቀረበው ሪፖርትም አመራሩ በአግባቡ ገምግሞና ከዚህ ቀደም የተሰጡትን ግብረ መልሶች አካቶ አልቀረበም ነው" ያሉት።

ይህ ደግሞ በተቋሙ ነባርና አዲስ አመራሮች ላይ ተናቦ ያለመስራት ችግር እንዳለ አመላካች መሆኑን ወይዘሮ አበባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ወይዘሮ አበባ እንዳሉት በቀረበው ሪፖርት ሚኒስቴሩ ከሚከታተላቸው ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት በኩል ክፍተት አለበት።

በቀረበው ሪፖርትና የተቋሙ አመራሮች በሰጡት ምላሽ ላይ የሀሳብ ልዩነት መኖር እንዲሁም በሪፖርት አሰራር ላይ የታየው ክፍተት ለተቋሙ ቀጣይ ሥራ ተግዳሮት ስለሚሆን በአፋጣኝ መፈታት እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የቀረበው የሩብ ዓመት ዕቅድ በርካታ ክፍተቶች ስላለበት ቋሚ ኮሚቴው ተከልሶ እንዲመጣም አዟል።

ወይዘሮ አባበ እንዳሉት ተቋሙን በኃላፊነት እየመሩ ያሉ አዲስ አመራሮች ቢሆኑም ነባር ባለሙያዎች ሥራዎችን ማገዝና ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።

"ሚኒስቴሩ በተለያዩ የፌደራል ተቋማት የሚገኙ ሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት እንደ ሌሎች ዘርፎች በተሟላ የሰው ኃይል እየተደራጁ መሆናቸውን እንዲሁም በቂ በጀትና ምቹ የሥራ ሁኔታ ስለመፈጠሩም መከታተልና ማጠናከር ይገባዋል" ብለዋል።

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ " በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር ይሰራል" ብለዋል።

በተለይ በኮቪድ-19 ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን ከተቋማት ጋር በቅንጅት የመስራትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ ነው የገለጹት።

ወጣቶች ለመብቶቻቸው እንዲሟገቱና የህጻናትና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም