ሳዑዲ ዓረቢያ ለኢትዮጵያ የቴምር አልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ሳዑዲ ዓረቢያ ለኢትዮጵያ የቴምር አልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 ኢትዮጵያ ለተጨማሪ አልሚ ምግብ የሚውል የ100 ቶን ቴምር ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ድጋፍ ተደረገላት። በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና በሳዑዲው አምባሳደር አብዱላህ ፋሌህ መካከል የድጋፍ ርክክቡ ተፈጽሟል። በኢትዮጵያ የሳዑዲው አምባሳደር አብዱላህ ፋሌህ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ከሚያከናውኑት ተግባራት መካከል ነው። ድጋፉ በሰዑዲው ንጉስ ሰልማን የበጎ አድራጎትና ድጋፍ ማዕከል አማካኝነት የቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳመነ ዳሮታ በድርቁም ወቅት ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጎን ያልተለየች መሆኗን በመግለጽ አሁን ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል። ቴምሩ በኢትዮጵያ የምግብ ድጋፍ ለሚፈልጉ ተጨማሪ አልሚ ምግብ በመሆን እንደሚከፋፈልም አስታውቀዋል። በድጋፍ የተሰጠው ቴምርም ከጥራት አንፃር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ክትትል የተደረገበት ሲሆን በውስጡ አልሚ ማዕድናትን የያዘ ነው ተብሏል። በዋናው የስንዴና የበቆሎ ምግብ ቶሎ አቅም መመለስ ለማይችሉ ተጎጂ ሰዎች ቴምሩ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል። ድጋፉ አዳማ ወደሚገኘው የኮሚሽኑ ዋና መጋዘን በመግባት ላይ ይገኛልም ተብሏል። በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ድጋፍ በመደበኛ ፕሮግራም እየተደረገላቸው ሲሆን በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ለተፈናቀሉ 2 ሚሊዮን ዜጎች በኮሚሽኑ ተጨማሪ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ነው የተገለፀው።