በፅንፈኛው የህወሃት ታጣቂ ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ለዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ተጠናክሮ ቀጥሏል- የኢፌዴሪ አየር ሃይል - ኢዜአ አማርኛ
በፅንፈኛው የህወሃት ታጣቂ ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ለዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ተጠናክሮ ቀጥሏል- የኢፌዴሪ አየር ሃይል
አዲስ አበባ ህዳር 2/2013 (ኢዜአ) የኢፌዲሪ አየር ሃይል በፅንፈኛው የህወሃት ታጣቂ ቡድን ላይ የሚወስደው ህግ የማስከበር እርምጃ ለዜጎች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ኢላማውን ጠብቆ እየተካሄደ መሆኑን የአየር ሃይሉ ዋና አዛዥ ገለጹ።
የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰተዋል።
በመግለጫቸውም በፅንፈኛው የህወሃት ታጣቂ ቡድን ላይ በአየር ሃይሉ እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ በውጤታማነት ቀጥሏል ብለዋል።
ከሳምንት በፊት ጁንታው በሰሜን እዝ የመከላከያ ሃይል ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የኢፌዴሪ አየር ሃይል በፍጥነት ግዳጅ ተቀብሎ ህግ የማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የፅንፈኛው ህወሃት ታጣቂ ሃይል ሊጠቀምባቸው ያሰባቸውን የተመረጡ ኢላማዎች በመደብደብ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን ገልጸዋል።
አየር ሃይሉ የታጣቂ ቡድኑን ይዞታዎችና የተመረጡ ቦታዎች በመለየት ኢላማዎችን ጠብቆ በወሰደው እርምጃ የተሳካ ጥቃት መፈፀሙን ነው ዋና አዛዡ የገለጹት።
ፅንፈኛው ቡድን ከሰሜን ዕዝ ተቆጣጥሮት የነበረው ሚሳኤልና ራዳርም በፍጥነት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።
በተለይ ጠላት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ኢላማዎች ስትራቴጂክ መሳሪያዎች ያሉበት ራዳሮችና ሚሳኤሎች የነዳጅ ዴፖዎች እንዲሁም መሳሪያ ማከማቻዎች ጥንቃቄ በተሞላበት እንዲወድም ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም አየር ሃይሉ በፅንፈኛው ቡድን ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አብራርተዋል።
“ጽንፈኛ ቡድኑ በየዕለቱ የሚያሰራጨው የሃሰት ወሬም ቡድኑ በውሸት ተፈጥሮ በውሸት የኖረና ከነውሸቱ የሚቀበር መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።
አየር ሃይሉ በፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ላይ የሚያደርገውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሜጀር ጄኔራል ይልማ አረጋግጠዋል።