ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ዝግጅት እያደረገች መሆኗን የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ገለጸ

አዲስ አበባ ሃምሌ 10/2010 ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም የሚያስችላትን ዝግጅት እያካሔደች መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር ወይዘሮ የሺ ፈቃደ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት በተስማሙት መሰረት ወደቡን ለመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከዚህ ውስጥም ኢትዮጵያ በምን መልኩ ወደቡን መጠቀም እንደምትችል የመጠቀሚያ ስምምነቶችን ለመፈረም አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች እየተዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ እስከ አሁን በርበራና ጅቡቲ ወደቦችን ስትጠቀምበት እንደነበረችው ሁሉ የአሰብ ወደብንም ለመጠቀም ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ መሆኗን ተናግረዋል። እንደ ወይዘሮ የሺ ገለጻ በተጨማሪ ደግሞ ባለስለጣኑ ከወደብ አጠቃቀሙ ስምምነት ዝግጅት በተጨማሪም ወደቡ አሁን ባለበት ሁኔታ ለመጠቀም የድርጊት መረሃ ግብር እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህም ባለስልጣኑ በጋራ ከሚሰራቸው እቃ አመላላሽች አስመጪዎች ከወደብ እቃ የሚያነሱ የፍተሻና የጉምሩክ ፣የሚዛን አገልግሎቶችን  ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን ከሚያከናውኑ አካላት ጋር በትብብር እንየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የወደቡ አሁን ያለው የማስተናገድ አቅሙም ከድርጊት መርሐ ግብሩ የሚካተትና ጥናት ላይ ያለ ነው ያሉት ወይዘሮ የሺ ይኸው ስራ ሲጠናቀቅ ደረጃ በደረጃ ባለው አቅም ወደ አገልግሎት የሚገባበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል። ስምምነቱና የድርጊት መርሐ ግብር ዝግጅቱ ተጠናቆ በሁለቱ አካላት እንደተፈረመም ወደ ስራ እንደሚገባ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። አሰብ ወደብ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጋር ወደ ግጭት እስከገቡበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ዋነኛ የወጪና ገቢ እቃዎች ማስተናገጃ ወደብ ሆኖ ያገለግል ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም