ቀጥታ፡

የህወሐት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት የሀገር ክህደት ወንጀል ነው -- ምሁራን

አዳማ ህዳር 2/2013 (ኢዜአ) የህወሐት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት የሀገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ ለፍርድ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት ሊያገኝ ይገባል ሲሉ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

"የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የሰነዘረ የጥፋት ቡድን ለውጭ ጠላት በር የከፈተ ነው"  ሲሉ ምሁራኑ ለኢዜአ አስታውቀዋል ።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማእከላት ዲን ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ እንደገለጹት ህወሐት በሀገር መከላከያ ላይ የወሰደው ጥቃት የሀገር ክህደት ወንጀል ነው።

"በመከላከያ ሰራዊት ጥቃት የሚፈጽም ኅይል በመካከላችን እያለ የሚኖር የፖለቲካ ጨዋታ የለም" ያሉት ዶክተር ዓለሙ  ቡድኑ ላደረሰው ጥቃት ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንደሚገባው አመላክተዋል ።

በህወሐት ቡድን የተፈፀመው ተግባር የሀገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ አጥፊዎቹ ለህግ እንዲቀርቡ መንግስትን መደገፍና ከመከላከያ ጎን መቆም አማራጭ የለሌው የሀገር ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመንግስት ጎን የምንቆመው ተጠይቀን ወይም በፍላጎት ብቻ ሳይሆን የህልውናችን፣ የልጆቻችንና በአጠቃላይ የሀገራችን  ጉዳይ በመሆኑ ነው" ብለዋል ።

በሀገሪቱ  በአራቱም ማእዘናት የሚኖረው ህዝብ ከመንግስትና ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ባለው አቅም ማገዝ እንዳለበት ጠቁመዋል።

"የሰሜን እዝ የሠራዊት አባላትና የመከላከያ ካምፖችን ያስጠቁ በመከላከያ ከአመራር እስከ ታችኛው ኅይል ድረስ ያሉ የህወሃት የጥፋት ቡድን ቅጥረኞችን ከመዋቅሩ ማፅዳትና በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

"መንግስት የጥፋት ቡድኑን ጨምሮ ለእያንዳንዱ ተባባሪና ፈፃሚ የሚገባቸውን ፍርድ በመስጠት ለአንዴና ለመጨራሻ ጊዜ በየቦታው የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ማስወገድ አለበት" ብለዋል።

"ከውጭ የሚመጣን ጠላት ከህዝብና ከሀገር የሚጠብቅ መከላከያን ማጥቃትና ለጠላት አጋልጦ መስጠት አሳፋሪ ተግባር ከመሆኑም ባለፈ አንገታችንን ያስደፋን ነው" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ምህንድስና መምህር ዶክተር ኬይረዲን ተማም ናቸው።

ለሀገር በሚዋደቅና በሚሞት መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈፀመው አሳፊሪ ተግባር መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት ያገኘበት ክስተት መሆኑን ጠቁመዋል።

"መንግስት ሀገርን ለማዳንና የህዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በገንዘብ፣ በእውቀትና እስከ ህይወት መስዋዕትነት መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።

"ለእኛ ብሎ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የማይገኝበት ጫካ ወስጥ የሚኖረውን ሠራዊት ማገዝ አሁን ነው" ብለዋል።

"የአካባቢያችንን ሰላም ነቅተን በመጠበቅ  ሀገራችንን ከአውሬ መጠበቅ ይገባናል" ሲሉ ዶክተር ኬይረዲን  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም