ቀጥታ፡

ሰራዊቱ እያካሄደ ያለውን የህግ ማስከበር ተግባር ለማገዝ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ጎንደር/ደብረ ማርቆስ /ደብረ ብርሃን ህዳር 2/13 (ኢዜአ) በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በአማራ ክልል ልዩ ኅይል እየተካሄደ ያለውን የህግ የበላይነት የማስከበር ተግባር ለማገዝ በአማራ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፎች እየተደረጉ ነው። 

ከክልሉ ምስራቅ ጎጃምና ሰሜን ሸዋ ዞኖችም በገንዘብና በአይነት የ13 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰብሰቡ ተነግሯል።

በክልሉ ባለሀብት የሆኑት አቶ ወርቁ አይተነው የህግ ማስከበር ተግባሩን በስንቅ ለመደገፍ 100 ሰንጋዎችንና 200 ኩንታል የፊኖ ዱቄት አበርክተዋል፡፡

የባለሀብቱ ተወካይ አቶ ሲሳይ ታደሰ በባለሀብቱ የተደረገውን የስንቅ ድጋፍ ለማእከላዊ ጎንደር ዞን የሎጅስቲክ ኮሚቴ ዛሬ አስረክበዋል፡፡

ተወካዩ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የክልሉ ልዩ ኅይል በትህነግ ጽንፈኛ ቡድን ላይ እየወሰዱ ያለውን ህግ የማስከበር ስራ ለማገዝ ባለሀብቱ ድጋፉን አድርገዋል።

ሰራዊቱና የክልሉ ልዩ ኅይል ከመንግስት የተሰጣቸውን ግዳጅ በስኬት እስኪያጠናቅቁ ድረስም ድጋፋቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ቃል መግባታቸውን ተወካዩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለክልሉ ልዩ ኅይል ስንቅ የሚውል 60 ኩንታል በሶ በተወካያቸው አማካኝነት ዛሬ ለሎጅስቲክስ ኮሚቴው አስረክበዋል፡፡

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሎጅስቲክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ባንቲሁን መኮንን ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ህብረተሰቡና ባለሀብቶች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊቱና ለክልሉ ልዩ ኅይል ያላቸውን ህዝባዊ ወገንተኝነት የሚያሳይ ነው ፡፡

ኮሚቴው ከህብረተሰቡና ከባለሀብቶች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ በተቀናጀ መንገድ በማስተባበርና በየእለቱ በግንባር በመገኘት ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለክልሉ ልዩ ኅይል እያስረከበ ይገኛል ብለዋል ።

በምስራቅ ጎጃም ዞንም ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለክልሉ ልዩ ኅይል ድጋፍ የሚውል  በገንዘብና በአይነት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታውቋል ።

የጽህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ወይዘሮ አዲሴ ጫኔ ለኢዜአ እንደገለጹት ከሀዲው የህወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ ለማገዝ ድጋፍ እየተሰበሰበ ነው።

እስካሁን ህብረተሰቡን በማስተባበር በጥሬ ገንዘብ 8 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸው 2 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው  ሰንጋዎች፣  በግና ፍየሎች፣ ጤፍና ሌሎች ቁሳቁሶች ደግሞ በድጋፍ መገኘታቸውን አመልክተዋል ።

ድጋፉን የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ኅላፊዋ የዞኑ አመራር የወር ደመወዙን 25 በመቶ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑን አስታውቀዋል ።

ከክልሉ ሰሜን ሽዋ ዞንም  ለተመሳሳይ ዓላማ የሚውል 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ መሰብሰቡን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ ገልጸዋል።

"የህዝብንና የሀገርን ደህንነት ከመጠበቅ በተጓዳኝ በማንኛውም ልማት የሚሳተፍ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የእናት ጡት ነካሾች በፈፀሙት ጥቃት የዞኑ ህዝብ  አዝኗል " ብለዋል ።

''የመከላከያ ሰራዊታችን ጥቃት የመላው ኢትዮጵያዊያን ጥቃት ነው'' በሚል አርሶ አደሮች፣ ባለሀብቶችና የመንግስት ሰራተኞች በገንዘብና በአይነት ድጋፉን ማድረጋቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም