ቀጥታ፡

ከጥፋት ኃይል ነጻ የወጡ አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋምላቸዋል -- የመከላከያ ሚኒስትሩ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 02/2013 (ኢዜአ) ከፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን ነጻ የወጡ የትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋምላቸው መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ ገለጹ።

ሚኒስትሩ የአገር መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል በፅንፈኛው የህወሃት ጁንታ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ቡድኑ በአምስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ሓሰተኛ መረዎችን እያሰራጨ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የሕግ የማስከበር እርምጃ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እየተደረገ ያለ ጦርነት የማስመሰል አዝማሚያ መኖሩን ጠቅሰዋል።

የአጎራባች ክልሎች ግዛት ማስፋፋት ማስመሰል፣ ፅንፈኛው ሃይል የፈፀመውን ክህደት ተራ ወንጀል አስመስሎ ማቅረብ፣ ሰራዊቱ በንጹሃን ዜጎችና በመሰረተ ልማት ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው በሚል የሐሰት መረጃ እንደሚያሰራጩ ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ መረጃዎቹ ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ህዝቡ መረዳት እንዳለበት አስገንዝበው፤ የሃሰት ወሬዎችን የሚያሰራጩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ሃሰተኛ መረጃ በመፍጠር ወደ ማወናበድ መግባቱ የማሴርና የማደናገር ተፈጥሯዊ ባህሪው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ የሚገኘው መከላከያ ሰራዊቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወንጀለኛ ቡድኑን በቁጥጥር ስር አውሎ ለሕግ እንደሚያቅርብ አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም “በትግራይ ክልል ከፅንፈኛው ሃይል ነጻ የወጡ አካባቢዎችን እንዲሁም እጅ የሚሰጡ ታጣቂዎች ጉዳይ በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመ ኮሚቴ እየተመራ ነው” ብለዋል።

ከቡድ ነጻ የወጡ የትግራይ አካባቢዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የሕዝቡን ደህንነት የመጠበቅና የማደራጀት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተጨማሪም “ለአካባቢው ነዋሪዎች ስልጠናዎችን በመስጠት በማደራጀትና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ የእለት ተእለት ስራቸውን ማከናወን እንዲጀምሩ ይደረጋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም