ቀጥታ፡

"የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን አገር የማዳን ተልዕኮ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ያጠናቅቃል" -የመከላከያ ሚኒስትር

አዲስ አበባ ህዳር2/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን አገርን የማዳን ተልዕኮ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ ገለጹ።

ሠራዊቱ ለኦፕሬሽኑ በቂ ትጥቅና አቅም አለው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር ስራ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር ቀነዓ በዚሁ ወቅት  "የአገር መከላከያ ሠራዊት የጦርነት ስትራቴጂ ግልጽ ነው። በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ በአነስተኛ ኪሳራ 360 ዲግሪ በመዋጋት በምድርም በአየርም ታርጌቶችን መሰረት በማድረግ ይሰራል" ብለዋል።

በክልሉ የሚካሄደው ኦፕሬሽን ውስብስብና በዕቅድ ውስጥ ያልነበረ ከመሆኑ አንጻር የወሰደው ጊዜ ረጅም የሚባል እንዳልሆነም ተናግረዋል።

"የአገር መከላከያ ሠራዊቱ የተሰጠውን አገር የማዳን ተልዕኮ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈጽማል" ብለዋል።

የጦር መሳሪያዎች መቃጠላቸው የሠራዊቱ አቅም ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚባለው ነገር ከእውነት የራቀ መሆኑንና ሠራዊቱ ኦፕሬሽኑን ለማከናወን በቂ ትጥቅ፣ አቅምና ኃይል እንዳለው ነው ዶክተር ቀነዓ ያስረዱት።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ ሠራዊቱ በትጥቅ፣ በዝግጁነትና በአደረጃጀት በጠንካራ ቁመና ላይ ይገኛል።

ሠራዊቱ አገሩንና ሕዝቡን ከጥፋት የሚጠብቅበት ዓላማ ያለው ሠራዊት መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ሠራዊቱ ካለበት አካባቢ አንዳንድ ቦታዎችን ለተልዕኮ ለቆ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የክልል የጸጥታ ኃይሎች የተለቀቀውን ቦታ እንዲረከቡ ከክልሎች ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የህወሓት የጥፋት ቡድን ካለው ባህሪይ አንጻር ዜጎችን እንደ ጋሻ አድርጎ ንጹሀንን ሰለባ ሊያደርግ ይችላል ያሉት ዶክተር ቀነዓ፣ ዜጎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ሠራዊቱ ጥብቅ ክትትል ያደርጋል ብለዋል።

ኦፕሬሽኑን አስመልክቶ በተከታታይ ለመገናኛ ብዙኃንና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ገለጻዎች እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ሠራዊቱ ከኦፕሬሽኑ መጠናቀቅ በኋላ ሕዝቡን የማረጋጋትና ደህንነቱን ለመጠበቅ እንደሚሰራም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም