ቀጥታ፡

15ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል - አፈ ጉባዔ አደም ፋራህ

ሀዋሳ፤ ህዳር 01/2013 (ኢዜአ) 15ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ ገለጹ።

ህዳር 29 ለሚከበረው በዓል ማስጀመሪያ "የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ችቦ" ዛሬው በጅግጅጋ ከተማ ተለኩሷል።

ችቦውን አፈ ጉባዔ አደም በመለኮስ ለሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ አስረክበዋል።

በዓሉ ከዚህ ቀደም ሲከበር ከነበረበት ሁኔታ በተለየ መንገድ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ መርሐ ግብሮች እንደሚከበር ተገልጿል።

ከክንውኖች አንዱ የሆነው ከምስራቅ ኢትዮጵያ ተነስቶ በሁሉም ክልሎች የሚደርሰው "የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ችቦ" መርሐ ግብር እንደሆነ ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ የደም ልገሳና የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዓሉ የሚከበርባቸው ዋነኛ ሁነቶች ስለመሆናቸውም ተወስቷል።

በዛሬው መርሐ ግብር ላይ አፈ ጉባዔ አደም ፋራህና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ደም ለግሰዋል።አፈ ጉባዔ አደም ባደረጉት ንግግር “በዓሉ ሕገ መንግሥቱን ለማስተማርና ለማስረጽ ልንጠቀምበት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

"የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ችቦ" ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ሕብረ-ብሔራዊነት፣ እኩልነትን፣ አንድነትንና ሰላምንና ተስፋን ጨምሮ የሕዝቦች ትስስርና የኢትዮጵያ ቀጣይነትን እንደሚያመለክት ገልጸዋል።

በዘንድሮ በዓል የደም ልገሳና የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የመስጠት ሁነት እንደሚካሄድ የገለፁት አፈ ጉባኤው፤ የዘንድሮ በዓል ዓላማውን ባሳካ መልኩ እንዲከበር ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ትርጉም ከለውጡ በፊት የነበረው አተገባበር የይስሙላ እንደነበር አስታውሰዋል።

ዘራፊው የህውሀት ቡድን የህዝቦችን የብሄር የሃይማኖት እና የአመለካከት ልዩነቶች ተጠቅሞ አገር ለማፍረስ እና ለመበታተን ሲሰራበት እንደቆየ ተናግረዋል።

የብሄር መብት ብሎ ለይስሙላ ሰጥቶ ሁሉንም ብሄረሰቦች ሲጨቁን የነበረና በዓሉንም ለተራ ፕሮፖጋንዳ ማስፈፀሚያ አድርጎ ሲንቀሳቀስ እንደነበር አመላክተዋል።

“ትናንት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የሚገባቸውን መብት ራሱን እንደሰጪ አድርጎ ሲመለከት የነበረው ይህ ዘራፊ ቡድን አሁን ደግሞ የመከላከያ ሀይል ላይ ጥቃት አድርሷል” ብለዋል።

የዘንድሮ በዓል አከባበር ልዩ የሚያደርገው በዚህ ዘራፊ ቡድን ላይ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በ15ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም