በዛሬ ውሎ በምእራብ ትግራይ ግንባር በርካታ የህወሃት ታጣቂ ቡድን አባላት ተደምስሰዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዛሬ ውሎ በምእራብ ትግራይ ግንባር በርካታ የህወሃት ታጣቂ ቡድን አባላት ተደምስሰዋል
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) የአገር መከላከያ ሰራዊት በምእራብ ትግራይ ግንባር በህወሃት ታጣቂ ሃይል ላይ ዛሬ በወሰደው እርምጃ በርካታ የታጥቂ ቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውን የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል በላይ ስዩም ገለጹ።
ከተደመሰሱት በተጨማሪ 29 ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በዚሁ ግንባር ቡድኑ ከፍተኛ ቁሳዊ ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን 115 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 11 መትረየስ፣ 2 ድሽቃ፣ 8 አር ፒጂ ከባድ መሳሪያ መማረኩን ገልጸዋል።
በምእራብ ትግራይ ግንባር በዛሬው እለት 152 የእጅ ቦንብ፤ 2 ስናይፕር፣ 4 ኤም-14 ጦር መሳሪያ፣ 2 ኢንኮም ሬድዬ፣ 21 ሺህ 65O የክላሽ ጥይት፣ 14 ሺህ 73O የመትረየስ ጥይትም የመከላከያ ሃይሉ በእጁ አስገብቷል።
በአውደ ውጊያው 1 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 64 የጦር ሜዳ ቀበቶ፤ 6 የአር ፒ ጂ ቅንቡላ፣ 90 የክላሽ መካዘን እና 10 የመትረየስ ዝናር ከጠላት ሃይል መማረኩ ይፋ ተደርጓል።
ከሰሜን እዝ 5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ተዘርፈው የነበሩ 5 ታንኮችንም ማስመለስ ሲቻል አንዱ ተመቶ መቃጠሉ ተገልጿል።
የሰሜን እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል በላይ ስዩም እንዳሉት፤ ህግን የማስከበር ዘመቻው በስፋት እና በድል ተጠናክሮ መቀጠሉንና በርካታ ቦታዎችንም መቆጣጠር እንደተቻለ አመልክተዋል።