ከህወሓት ተልዕኮ ወስደው በሲዳማ ክልል ጥፋት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከህወሓት ተልዕኮ ወስደው በሲዳማ ክልል ጥፋት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
ሀዋሳ፤ ህዳር 01/2013 (ኢዜአ) ከህወሓት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ ወስደው በሲዳማ ክልል የህዝቡን ሰላም ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ የህወሓትን የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን በርዕሰ መስተዳደሩ የሚመራ ዐቢይ ኮማንድ ፖስት ተደራጀቶ እየሰራ መሆኑን ተናገረዋል።
ከክልሉ የፀጥታ አካላት ፣ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ የፌዴራል ፖሊስና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት በአባልነት ያቀፈው ኮማንድ ፖስቱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት በትኩረት እየተከታተለና እየተቆጣጠር ነው ብለዋል።
እስካሁን በቅንጅት ባደረጉት የቁጥጥር ሥራም ከህወሓት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ ተቀብለው በክልሉ በተለይ ሀዋሳ ከተማ የተለያዩ ጥፋቶችን ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ 25 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታወቀዋል።
ከነዚህ ውስጥ አምስቱ የኦነግ ሸኔ አባላት እንደሆኑ ጠቁመው፤ ሌሎቹ በቀጥታ ከህወሓት ቡድን ተልዕኮ ወስደው ወደ ክልሉ የገቡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል በተለይ በሀዋሳ ከተማ በሆቴል ውስጥ ተሸሸገው የብሔር ግጭት ለመቀስቀስና ለዚህም ስምሪት ለመስጠት ወጣቶችን ሲመለምሉ የነበሩ መኖራቸውን ተናግረዋል።
የክልሉን ሰላም ለማወክ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች መያዛቸውንም አቶ አለማየሁ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ከ36 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ የብር ኖቶች ፣ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ82 በርሜል በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት በቀጣይም የህብረተሰቡ ሥጋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ እየሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊ፤ ከዛሬ ጀምሮ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪና ባለ ሁለት እግር ሞተር ተሽከርካሪ በክልሉ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን አስታውቀዋል።
በተለይ ባለሁለት እግር የሞተር ብስክሌት ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ከአሽከርካሪው ውጭ ሌላ ሰው መጫን እንደማይፈቀድ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል የፀጥታ ኃይል ለ27 ዓመታት ህዝብን ሲጨቁን የነበረውን ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በማንኛውን ጊዜ የመንግስትን ጥሪ ለመቀበልና እስከ ግንባር ድረስ ተሰልፎ ለመዋጋት የአካልም የሥነ ልቦናም ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ፀጉረ ልውጥ ግለሰቦችና እንግዳ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በሚመለከትበት ወቅት ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ትብብር እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።