ቀጥታ፡

የትህነግ ባለስልጣኖች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ህግ ማስከበሩን ማጠናከር ይገባል- የትግራይ ተወላጆች

ጎንደር፣ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) የትግራይን ህዝብ ለአደጋ ያጋለጡት ወንጀለኛ የትህነግ ባለስልጣኖች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በጎንደር ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አስታወቁ፡፡

የከተማው አስተዳደር የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የመከረ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉ የትግራይ ተወላጅ ነዋሪዎች መካከል አስር አለቃ ገብርዬ አብርሃ እንደገለጹት ትህነግ በሀገሪቱ ለተፈጸሙ የዘረኝነት ጥቃቶችና በደሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጁን የነከረ ወንጀለኛ ቡድን ነው፡፡

''ትህነግ የትግራይን ህዝብ የማይወክል የዘረኞች ቡድን ነው'' ያሉት አስር አለቃ ገብርዬ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ ይገባል" ብለዋል፡፡

"ትህነግ የኢትዮጵያ ህዝቦች አለኝታና መከታ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ሀገርና ህዝብን የመክዳት ከፍተኛ የጦር ወንጀል ነው" ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ነዋሪና የብሄሩ ተወላጅ ኮሎኔል ኪሮስ ኪዳኔ ናቸው።

መከላከያ ሰራዊት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተልእኮ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ትግራይን ከወንጀለኛ ቡድኑ ነጻ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

"እኛም ትግራይ ከወንጀለኛ ቡድኑ ነጻ የምትሆንበትን እለት እየናፈቅን ነው" ብለዋል ።

በጎንደር ከተማ ከ32 አመት በላይ መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ገብረመድህን በላይ በበኩላቸው "በትህነግ የወንጀለኛ ቡድን እኩይ ሴራ የትግራይ እናት ዛሬም በልጆችዋ ለዳግም የለቅሶ እምባ መዳረጓ ያሳዝነኛል " ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"የትግራይ ህዝብ ለትህነግ ወንጀለኛ ቡድን የስልጣን ማራዘሚያ በመሆን አላግባብ ህይወቱንና ንብረቱን መገበር የለበትም" ነው ያሉት ።

የትግራይ ህዝብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል ።

"ከዘረኝነትና ከከፋፋይነት ውጪ ሌላ አላማ የሌለውን ትህነግ እየተፋለመ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደሜን ለመለገስም ሆነ አቅሜ በፈቀደ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪና የብሄሩ ተወላጅ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ ናቸው፡፡

የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር ጎን ለጎን አንበጣ በመከላከልና ሰብል በመሰብሰብ በጎ ተግባር ባከናወነውና የክፉ ቀን ደራሽ በሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ትህነግ የፈጸመው ክህደትና ጥቃት ታሪክ ይቅር የማይለው ጠባሳ ነው" ብለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኅላፊ አቶ ሞላ መልካሙ መከላከያ ሰራዊት በትህነግ ጽንፈኛ ቡድን ላይ የጀመረው ህግ የማስከበር ስራ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ በከተማው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

"ትህነግ የአማራና የትግራይ ወንድማማች ህዝቦች እንዲነጣጠሉና እንዲጋጩ በርካታ ሴራዎችን በስውርም ሆነ በግልጽ ሲያከናውን ቆይቷል" ብለዋል ።

የብልጽግና ፓርቲ በከተማው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ መብታቸው ተከብሮላቸው ያለስጋትና መሸማቀቅ የቀደመ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ኅላፊው አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም