ቀጥታ፡

መንግስት እያከናወነ ያለው ህግን የማስከበር እርምጃ ዘላቂ ሠላምን ይገነባል - ምሁራን

ደሴ/ደብረማርቆስ ህዳር 01/2013(ኢዜአ) መንግስት ህግን ለማሰከበር በህወሓት ጽንፈኛ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የሀገሪቱን  ዘላቂ ሠላም እንደሚገነባ የወሎና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ተናገሩ፡፡

በወሎ ዩነቨርሲቲው የሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ጥቃት በየትኛውም ዓለም ተሰምቶ የማይታወቅ አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡

ይህ የጥፋት ኃይል ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት የሃሰት ትርክት በመፍጠር ህዝብ ከህዝብ ሲያስጨፈጭፍና ሲያፈናቅል የነበረውን የመጨረሻ ሴራ ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡

ከመንበረ ስልጣኑ ከተገፋ በኋላም ከጥፋት ድርጊቱ ሊቆጠብ ይችላል ተብሎ ቢታሰብም ይባስ ብሎ ከወጭ ጠላት ጋር በመተባበር በሠራዊቱ ላይ በፈጸመው ጥቃት የሀገራችን ሉዓላዊነት ተዳፍሯል ብለዋል።

መንግስት እየወሰደው ያለው ህግን የማስከበር እርምጃ ለሃገር ሰላምና መረጋጋት የሚበጅና ለትግራይ ህዝብም እፎይታን የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናገረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ደሙን አፍስሶ ያመጣው ለውጥ አይቀጥልም በሚል የታወረ አመለካከት ተስፋ የቆረጠው ጽንፈኛው ቡድን የመጨረሻ ጥይቱን መተኮስ ጀምሯል ነው ያሉት፡፡

ህወሓት በህዝብ ላይ ሲፈጽም የነበረውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሃብት ዝርፊያና የስልጣን መባለግ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማስቆም ተግባር የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ደጀን የማነ በበኩላቸው አሸባሪው የህወሓት ቡድን ላይ የተወሰደው ርምጃ ፍትሃዊ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ የኢትዮጵያ ህዝብ መገለጫና የሃገር አለኝታ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት ሊወገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ጽንፈኛው ቡድን ለረጅም ጊዜ ጉዳዩን በውይይት እንዲፈታ እድል ቢሰጠውም እንዳልተጠቀበት ጠቁመው፤ ራሱ በለኮሰው እሳት መለብለብ ሲጀምር የድርድር ፍላጎት ማሳየቱ ተቀባይነት የሌለው ከንቱ ቅዠት መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ለህግ በማቅረብ ወደ መደበኛ ስራውና ልማቱ እንዲመለስም ምሁራኑ ድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

የሐሰት ወሬ እየለቀቁ ህዝብ በሚያወናብዱ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይም የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ምሁራን መካከል የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ስማቸው አካሉ በሰጡት አስተያየት የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የተሰማራ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት አስነዋሪና ሊወገዝ የሚገባው ነው።

መንግስት በጽንፈኛው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለትግራይ ንጹሃን ዜጎች ጥንቃቄ በማድረግ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የህወሃት የጥፋት ቡድን በፊትም ለህዝብ ሃላፊነት የሌለውና የሀገሪቱን አንድነት ተጽዕኖ ውስጥ እንዲወድቅ ሲሰራ የኖረ ክፉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የህብረተሰብ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አስናቀ በቃሉ ናቸው።

የጥፋት ቡድኑ በሃገሪቱ ታሪክ ይቅር የማይባል ክህደት በመፈፀሙም በማንኛውም መለኪያ ወደ ድርድር የሚመጣበት አግባብ መኖር እንደሌለበትም ተናግረዋል።

የዚሁ ትምህርት ክፍል መምህር ይርጋለም ቢምረው በበኩላቸው የትግራይ ህዝብ በወገናቸው ደም የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚጣጣሩትን ሴረኞች ተንኮል ከመንግስት ጋር በመሆን ማክሸፍ ይኖርበታል ብለዋል።

ትህነግ ከመጀመሪያው ጀምሮ በፖለቲካ ሴራ ሃገርን የመነጣጠልና አንድነትን የማፍረስ ግብ ይዞ ላለፉት ዓመታት ሲሰራ እንደኖረና አሁን በተጨባጭ ያሳየውም ይህንኑ ክህደቱን መሆኑን ገልጸዋል።

በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው ህግን የማስከበር ስራ እስከ መጨረሻው የድል ምዕራፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም