ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሥራ ዕድል አማራጮችን የማስፋትና የስብዕና ግንባታ ላይ ሊሰራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሥራ ዕድል አማራጮችን የማስፋትና የስብዕና ግንባታ ላይ ሊሰራ ይገባል
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) መንግስት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የሥራ ዕድል አማራጮችን በማስፋትና በሰብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።
ወጣቱ የጥፋት ኃይል መጠቀሚያ ከመሆን ጠያቂና ምክንያታዊ ሊሆን እንደሚገባም ተመልክቷል።
ህዳር የአፍሪካ የወጣቶች ወር "የወጣቶች ትርጉም ያለው እንቅስቃሴና ተሳትፎ የተሻለች አፍሪካን ለመገንባት" በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ መከበር ጀምሯል።
የአፍሪካ የወጣቶች ወርን ምክንያት በማድረግ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ዛሬ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የፓናል ውይይት አካሄዷል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ አፍሪካ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ወጣቶች እንዳሏትና በኢትዮጵያም 70 በመቶ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ወጣት መሆኑን ገልጸዋል።
"ከወጣቱ ጋር ተቀራርቦ መስራት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው" ያሉት ወይዘሮ ህይወት፤ ወጣቱን በአግባቡ ይዞ ለልማት ማሰለፍ ካልተቻለ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ጊዜ የጥፋት ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማደፍረስ ወጣቱን ኃይል ለዚህ እኩይ ተግባራቸው ሲጠቀሙበት እንደሚስተዋል አስታውሰው፤ ወጣቱ የጥፋት ኃይል መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ ጠያቂና ምክንያታዊ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
መንግስት በ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ ወጣቱን በኢኮኖሚ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ባለው ሥራ ወጣቱን በማሳተፍ የተጀመረውን አገራዊ የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጽጌረዳ ዘውዱ በበኩላቸው የወጣቶች ችግር በርካታና ውስብስብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎች መሬት ወርደው ለውጥ እንዲያመጡ ከተፈለገ የተጠናከረ የወጣት አደረጃጀት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
"የዘንድሮውን ህዳር የወጣቶች ወርን ስናከብር የወጣቶችን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለአገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ በማሰብ ነው" ብለዋል።
ወይዘሮ ጽጌረዳ እንዳሉት መንግስት ወጣቶች በማንኛውም የአገራቸው ጉዳይ ላይ ዳር ቆሞ ተመልካች ሳይሆኑ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት እድል መስጠት አለበት።
በእዚህም የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል አማራጮችን ማስፋትና የሰብእና ግንባታ ስራዎችን መስራት የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል።
በብሪትሽ ካውንስል የወጣቶች የአድቮኬሽን ባለሙያ የሆነው ወጣት አብይ ኃይለመለኮት በበኩሉ መገናኛ ብዙሃን ለወጣቶች የሚሰጡት ሽፋን አነስተኛና አሳታፊ አለመሆኑን ገልጿል።
"ወጣቶችን ያላሳተፈ የአንድ ወገን ብቻ ድምጽ የሚተላለፍበት በመሆኑ ወጣቱ ሀሳቡን በማህበራዊ ድረ ገጽ እንዲያራምድ በር ከፍቷል" ብሏል።
በመሆኑም ወጣቶች የለውጥ ሃዋርያ እንዲሆኑ ተገቢውን ቦታ መስጠት እንዲሁም "እኔ ልስራልህ፤ እኔ ልናገርልህ ከማለት ባለፈ የጉዳዩ ባለቤት ማድረግ ይገባል " ብሏል።
የአፍሪካ የወጣቶች ወር እ .ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በየዓመቱ ህዳር 1 ይከበራል።