በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን ለማጎልበት የሚረዱ የአስተምህሮ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን ለማጎልበት የሚረዱ የአስተምህሮ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ
ሠመራ፣ ህዳር 1/2013 (ኢዜአ) የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴትን ለማጎልበት የሚረዱ የአስተምህሮ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም፣ አብሮነትና ብዝሃነት አያያዝ ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በሠመራ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የአፋር ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ መሀመድ አወል ክልሉ እስካሁን ላለው የህዝቦች አብሮነትና ሠላም የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ይህም ግጭቶች እንዳይከሠቱ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
ግጭቶቹን ለማስነሳት ሴረኞች ምንም ዓይነት ሙከራዎች ሳያደርጉ ቀርተው ሳይሆን ህብረተሰቡ ከአብሮነት ያፈነገጠና መልካም እሴቶቹን የሚያጠለሹ እኩይ ተግባራትን መፈናፈኛ እንዳይኖራቸው በማድረጉ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እንዳይኖሩና ሠላም ተጠብቆ እንዲቀጥል የሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ለዚህም ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ ሀጂ መስኡድ አደም በበኩላቸው ሠላም፣ መከባበር፣ መደማመጥ፣ አብሮነትና ይቅርታ የጋራ ሃይማኖታዊ እሴቶች መሆናቸውን ተናግረው፤ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምዕመናንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለነዚህ እሴቶች ተገዥ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
ጉባኤው በሃገሪቱ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ የሠላም እሴትን በመገንባትና አብሮነትን በማጠናከር ብዘሃነትን ማዕከል ያደረገ አንድነት እንዲጎለብት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ለዚህም መዋቅሩን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ በመዘርጋትና ለህብረተረቡ ተደራሽ በመሆን ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶችን ለማጎልበት የሚረዱ የአስተምህሮ ስራዎችን እየተከወኑ ነው ብለዋል።
የአፋር ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በክልሉ የሠላም እሴት ግንባታ ላይ በመስራቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የሠመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በቆይታቸው ሠላማዊ መማር ማስተማር እንዲሰፍን ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
ይህን አስተማሪና በጎ ተግባራቸውን በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አንስተዋል።
የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሼክ መሃመድ ደርሳ እንደተናገሩት ጉባኤው በአካባቢው ላለው የህዝቦች አብሮነትና ሰላም ከክልሉ መንግስት ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል።
በቀጣይም ብሄርም ሆነ የሃይማኖት ብዝሃነት የአንድነታቸውና አብሮነታቸው እንቅፋት ሳይሆኑ ፈጣሪ የሰጣቸው ጸጋዎች መሆናቸውን ለትውልድ በማስተማር ሠላማቸው ተጠብቆ እንዲቀጥል ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
እስከ ነገ በሚቀጥለው የምክክሩ መድረክ ከክልሉ ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ ሀይማኖቶች መሪዎች ፣የሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች እየተሳተፉ ነው።