ከዱባይ ፈጣን ዕድገት ምን ልምድ ሊወሰድ ይችላል?

201

በመንግስቱ ዘውዴ /ኢዜአ/

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በዓለም የከተሞች እድገት ዙሪያ ምክክር እንዲደረግና ልምድ እንዲወሰድ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮግራሞችንና መድረኮችን ያዘጋጃል። ይህ የአለም ከተሞችን የሚያገናኘው አለም አቀፉ የከተሞች ወር የ30 ቀናት ዘመቻ የሚደረግበት ነው። በሚካሄዱ የምክክር መድረኮች ከተሞች ያሏቸውን መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ በትኩረት እንዲወያዩ ይደረግበታል።

ዘንድሮም “urban October” በሚል መሪ ቃል በጥቅምት ወር በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

ከተሞች ሁሉን አቀፍ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጠንካራ የመቋቋም አቅም ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል የዓለም መሪዎች 11 ግቦችን ነድፈዋል። እነዚህን ግቦች ለማሳካት የዓለም የከተሞች ወር በማስመልከት የሚዘጋጁ ምክክሮች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። መንግስታት ከተሞቻቸውን ለማልማት የሚያስችሉ የልማት አቅጣጫዎችን ሲነድፉ በዘርፉ ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ልምድ በመቅሰም ነው።

ኢትዮጵያ ልትለማ የምትችልባቸው በርካታ አማራጮችን በተፈጥሮ የተቸረች ሀገር ናት። ዋናው ጥያቄ እነኝህን የተፈጥሮ ስጦታዎች እንዴት ወደ ሀብትነትና ልማት እንቀይራቸው የሚለው ነው።  ኢትዮጵያን በየዘመናቱ ሲያስተዳድሯት የነበሩ መሪዎች የሀገሪቱን እድገት ለማሳካት የተለያዩ ሀገራትን ልምዶች ለመቅሰም እንደ ዘመኑና ሁኔታው ሲሞክሩ እንዲሁም  በተወሰነ መልኩም ቀምረው ሲጠቀሙበት መቆየታቸው ይታወቃል። የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ቀርጸው ተግብረዋል። ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ከተሞች በሚፈለገው ደረጃ እድገት ማምጣት አልቻሉም።

ዘንድሮ የተከበረውን የዓለም የከተሞች ቀን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ከተሞችን እድገት የሚያሳዩ ትንታኔዎችን የያዙ ጽሑፎች ለንባብ በቅተዋል። ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል አንዱ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ማእከል የሆነችው ዱባይ እንዴት በፍጥነት እንዳደገች የሚተነትን   ነው። ይህ ጽሑፍም የኢትዮጵያ ከተሞች ከተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ዋና ከተማ ከሆነችው ከዱባይ የ50 ዓመታት የልማት ጉዞና ውጤት መቅሰም የሚችሉትን ልምድ ለማመላከት ያስችላል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ቀደም ሲል የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት የነበረችና በፈረንጆቹ አቆጣጠር በታህሳስ ወር 1971 ነጻ የወጣች ሀገር ነች። በምስራቃዊው ፋርስ ባህረሰላጤ እና በአረብ ባህረገብ መሬት/Arabian Peninsula/ ላይ የተመሰረተችው ዱባይ ከሰባቱ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ግዛቶች አንዷ ስትሆን፤ ሃገሪቷንም በዋና ከተማነት እያገለገለች ትገኛለች።

የህዝብ ብዛቷም 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆኑ ከተለያዩ ሀገራት የተሰባሰቡ ናቸው። የከተማይቱ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት 109 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተጠጋ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወይም ከኬኒያ የውስጥ ሀገራዊ ምርት (ጂዲፒ) ጋር እኩል እንደሆነ ይነገራል።

ከበረሃማነት ወደ ንግድ ማዕከልነት በሚለው አምድ ላይ የዱባይ የልማት ታሪክ በተገለጸበት ጽሁፍ  የዱባይ ከተማ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ከነበረችበት የአሳ ማጥመጃ ወደብነት ከ50 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከልነት የተቀየረችበት መንገድ በጣም ፈጣን ነበር። ይህች ከተማ የፈጣን ዕድገቷ መነሻ እና የከተማዋ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዲፋጠን፣ የሸቀጦች ንግድ እና የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ከተማዋ እንዲሳቡ ያደረጋቸው ዋናው ጉዳይ እኤአ በ1966 የተገኘው የነዳጅ ሀብቷ እንደሆነ በጽሁፉ ላይ ሰፍሯል።

ነዳጅ ከአላቂ ሀብቶች የሚመደብ ማዕድን  በመሆኑ ዛሬ ላይ ይህ የነዳጅ ምርት ለሀገሪቱ ጂዲፒ ገቢ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከአንድ በመቶ በታች ሲሆን የከተማዋ ከፍተኛው የጂዲፒ ገቢ የሚሰበሰበው ከንግድ፣ ከሪል ስቴት ግንባታ፣ ከባንክ አገልግሎትና ከቱሪዝም ነው። ይህም ከተማዋ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሷን መረጃው ያመላክታል።

ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት የተለያዩ የረጅምና የአጭር ጊዜ የልማት ዕቅዶችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ብታደርግም የታሰበውን ያህል የዕድገት ውጤት ማስመዝገብ አልቻለችም። ካለፈው ጊዜ ይልቅ አሁን የህዝቦቿ የመልማት ጥማት ከዕጥፍ በላይ አድጓል። ምን አልባትም ላለፉት 50 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት በተለይ ከንጉሳውያን አገዛዝ ከተላቀቀችና ስልጣኑን ወታደራዊ መንግስት ከተረከበበት ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት «ዘመናዊ» የመንግስት አስተዳደር ወቅቶች ሀገሪቱ በልማቱ ረገድ ልትመራባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን አገዛዞቹ ከሚያራምዱት የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር በማስተሳሰር የልማት ዕቅዶችን ነድፈው ሲሰሩ ቆይተዋል፤ እየሰሩም ነው።

የደርግ መንግስት ሀገሪቱን ማስተዳደር ሲጀምር ይዞት የተነሳውን የህብረተሰባዊነት ወይም ሶሻሊዝም አስተምህሮ /ርዕዮተ-ዓለምን/ በስፋት በማቀንቀን፤ ለሰፊው ህዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ በመግለጽ፤ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዘርፎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ወይም ማሻሻያዎችን መውሰድ ጀመረ። ለምሳሌ የባለሀብቶችን የሀብት መጠን ጣራ መወሰን፣ የንግድ ስርዓቱ በራሱ በገበያው ሳይሆን በመንግስት እንዲመራ ማድረግ፣ በርካታ መሬትና ቤት ይዘው ከቆዩ ባለንብረቶች በመውረስ ቤት ለሌላቸው መስጠት፣ የመሰረተ-ትምህርት ዘመቻ እንቅስቃሴ እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል።

በወቅቱ የሀገሪቱን ልማት ያፋጥናል በሚል ተዘጋጅቶ ተግባራዊ የተደረገው ዕቅድ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ላለመቻሉ በዋና ምክንያትነት የሚጠቀሰው መንግስት ከሚከተለው ፖለቲካዊ አስተምህሮ (ርዕዮተ-ዓለም) የተቀዳ ስለመሆኑ ጉዳዩን ያጠኑ ምሁራን ይገልጻሉ።

ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም የመንግስትነት የስልጣነ መንበሩን ሲቆናጠጥ እንዲሁ “ለብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥቅም” እንደሚሰራ በዋናነትም ”ማህበራዊ መሰረቴ ሰፊው አርሶ አደር ነው፤ በመሆኑም የአርሶ አደሩን ህይወት በመሰረታዊነት ለማሻሻል እሰራለሁ” ማለቱ ይታወሳል።

የ2000 ዘመን (ሚሌኒየም) መግባትን ተከትሎ በሁለት ምዕራፎች በተከፈለና ለአስር ዓመታት በዘለቀ “የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” የሚል ሰነድ ተዘጋጅቶ ሲተገበር ነበር።

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በሁለት የአንደኛውና ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚል ተመንዝሮ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል። ለማሳያነትም በ5 ዓመታት ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ታቅዶ የነበረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እና ሌሎች የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክቶች፣ የግብርና ማዳበሪያ እና መሰል ፋብሪካዎች በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ነበሩ። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ደግሞ 10 የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶችና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው።

በሁለቱም የእድገትና የሽግግር እቅድ ምዕራፎች ውስጥ ለመተግበር ታቅደው ብዙም ውጤት ካላመጡ ዘርፎች መካከል የባቡር መስመሮች ግንባታዎችና የመኖሪያ ቤቶች ናቸው።

የባቡር መስመር ዝርጋታው ከአዲስ አበባ ጅቡቲ፣ ከአዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ እንዲሁም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመሮችን ብቻ ስራ ያስጀመረ ሲሆን፤ የቤት ልማት ፕሮግራሞቹ የሚፈለገውን ውጤት ሳያስገኙ አሁንም በአዲስ አበባ ውስጥ እየተገነቡ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን መንግስት ከ15 ዓመታት በፊት የከተማ ነዋሪውን የቤት ችግር በአጭር ጊዜ እቀርፋለሁ ብሎ ያቀደው የቤት ልማት ፕሮግራም ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ አይደለም ባይባልም፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኘውን አርሶ አደር ያለበቂ ግንዛቤ እና ካሳ ኑሮውን ከመሰረተበት መሬቱ እንዲፈናቀል መደረጉ ውጤቱና ጉዳቱ ቁልጭ ብሎ መታየት ከጀመረ አመታትን አስቆጥሯል።

ከላይ የተጠቀሰው ችግር የኢትዮያ ከተሞች ወደጎን ሲስፋፉና ወደላይ ሲያድጉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያለማካተታቸው በተቀየሰው ፖሊሲ እና በአፈጻጸሙ መካከል ያለውን ስህተት አጉልቶ ያሳየ መሆኑ ይገለጻል።

በዚህ ላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ያለመዘመንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መስፋፋት፣ ውስብስብ ቢሮክራሲ እንዲሁም ሙስና የከተሞችን እድገት ቀፍድደው ከያዙ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

«ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቶች የካበተች፤ ነግር ግን ያልበለጸገች ሀገር» መሆኗን የማይካድ እውነታ ነው። እድገቷን ለማፋጠን ከተፈለገ  ቀልጣፋ አገልግሎት ስርዓት መዘርጋት፣ የኢንቨስትመንት ተደራሽነትን ማስፋት፣ አመቺና ተደራሽ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ፤ ሰፊ የተማረ የሰው ሀይል አቅርቦት፤ የመልካም አስተዳደርና አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር የዓለም አቀፍ ባለሀብቶችና ኩባንያዎችን መሳብ፣ ከሙስና የጸዳ ቁርጠኛ የመንግስት አመራር፣ የማበልጸጊያ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ችሎታ መኖር ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይነገራል።

በዚህም መነሻነት ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ሀገሪቱ ያሏትን የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦችን ለማልማት ከእንቅልፏ የባነነች ይመስላል። ለዚህም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኋይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን ላይ በነበሩባቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ያሏትን የቱሪዝም ሀብት እንድትለይ የሰጡት ትኩረት፣ ያሳዩት ቁርጠኝነትና የወሰዱት እርምጃ ተጠቃሽ ነው። ለዚህም «ምድረ-ቀደምት» የሚለውን የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ የሚመራ መሪ ቃል ወይም ሎጎ እንዲቀረጽና አገልግሎት ላይ እንዲውል ማድረጋቸውን እዚህ ላይ መግለጽ አስፈላጊ ነው።

ለውጡን ተከትሎ ወደ ስልጣኑ የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ሀገሪቱ በተለይም (አዲስ አበባ) ያሏትን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህቦቿን በመለየት ወደ ሀገራዊ ወረትነት መቀየር የሚያስችላትን የተለያዩ የልማት ዕቅዶችን በማቀድ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሲከታተሉ ቆይተዋል።

በታላቁ ቤተ-መንግስት የተሰራው የአንድነት ፓርክ፣ በአራት ኪሎ አካባቢ የተገነባው የሸገር ፓርክና የወዳጅነት አደባባይ እንዲሁም በእንጦጦ ጥቅጥቅ ጫካና ተራራማ አካባቢ ላይ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክቶች አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው ተጠናቆ ለምርቃትና ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸው ጉልህ ማሳያ ናቸው።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ አገልግሎት መሸጋገር የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በማነቃቃትና ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምርና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዕድገት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ ታምኖበታል።

የፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጥራትና ጊዜ መጠናቀቅና ለአገልግሎትም ክፍት መሆን ሶስት ዋና ዋና ልምዶችን አስተምረው ያለፉ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ይጠቅሳሉ።  አንደኛ ሊለሙ የሚችሉ ሀብቶችን ወደ ወረት የመቀየር የአመራር ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት፤ ሁለተኛ የፕሮጀክት አመራር እና አስተዳደር ብቃት ሶስተኛ ደግሞ የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ ሊሆኑ ወደሚችሉ የሀገሪቱ  አካባቢዎች የማስፋት ስትራቴጂን መተግበር መቻል የሚሉት ናቸው።

ባለፈው አንድ ዓመት በአዲስ አበባ የሚታየውን የልማት እንቅስቃሴ እና ከዚህም በመነሳት ከአዲስ አበባ የተገኘውን ልምድ በማጥናት ወደ አማራ ክልል የጎርጎራ፤ በኦሮሚያ ክልል የወንጪና በደቡብ ክልል የኮይሻ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማስፋት የሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ መመልከት ኢትዮዽያ ያላትን ሁለንተናዊ ሀብቶችና ዕሴቶች ለይታ በመረዳት ወደ ስራ ለመግባቷ አመላካች ነው።

ኢትዮጵያ ያሏትን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማልማትና ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገሪቱ በመሳብ ሀብቶችን ወደ ሀገራዊ ወረት ለመቀየር ከዱባይ ከተማ የ50 ዓመታት የልማት ጉዞና ስኬት ልትማራቸው የሚገቡ መልካም ተሞክሮዎች በርካታ ናቸው።

የነጻ ገበያ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ በቂ መሰረተ-ልማት ማሟላት፣ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡና እሴት መጨመር በሚያችሉ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ዝቅተኛ ታክስ መጣል፣ መዋዕለ ነዋያቸውን በስፋት ለሚያፈሱ ባለሀብቶች ረዘም ላለ ጊዜ የግብር ክፍያ እፎይታን መስጠት፣ በቂ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ማመቻቸት፣ ከንግድ ትርፍ የሚገኝን የመንግስት ገቢን ዝቅ ማድረግ እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በቁርጠኝነት ማስተካከል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በዘርፉ ላይ የሚሰሩ ዓለም አቅፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት፣ ባለሀብቶችና ምሁራን፤ አሁን በኢትዮጵያ  እየተከናወኑ ያሉትን የልማት እንቅስቃሴዎች፤ ስላላት እምቅ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም፤ መልማት የሚችሉ የቱሪዝም መስህቦችና የመንግስት ቁርጠኝነት በተመለከተ እየሰጡ ያሉት ዕውቅና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻር ለሀገሪቱ ትልቅ ዕድል ነው።

ከነዚህ ተቋማት መካከል የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ኮንፈረንስ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት «ኢትዮጵያ ባላት አዎንታዊ የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታ በምሥራቅ አፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ቀዳሚዋ፤ ከአፍሪካ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከግብፅ፣ ከኮንጎና ከሞሮኮ ቀጥሎ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች አገር ነች» ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።

አሁን ላይ ሀገሪቱ ባሏት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅሟንና አማራጮቿን መነሻ በማድረግ፤ በማምረቻ፣ እሴት በተጨመረበት የግብርና ዘርፍ፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት የእስያ፣ የሰሜን አሜሪካ፣ የቻይና፣ የአውሮፓና የአውስትራሊያ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ወደ አገሪቱ እየገቡ መሆኑን በጥቅምት 2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ሀገሪቱ ያሏትን መልማት የሚችሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶቿን እንዲሁም የቱሪዝም መስህቦቿን ሙሉ በሙሉ አጥንታ መተግበር ብትችል፤ ኢንቨስትመንቱን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ምቹ መሰረተ-ልማት አውታሮችን ብትዘረጋ እንዲሁም ሌሎች  ባለሀብቶችን ሊስቡ የሚችሉ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ ብታደርግ የኢንቨስትመንት ተመራጭነቷንና የቱሪስት መስህብነቷን በማሳደግ አሁን የተመዘገበውን የቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅሟን በብዙ እጥፍ ማሳደግ የምትችልበት ትልቅ አቅም አላት።ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም